Fana: At a Speed of Life!

አየር መንገዱ በቻድ ያለምንም ችግር በረራውን እንዲቀጥል የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቻድ ያለምንም ችግር በረራውን እንዲቀጥል የሚያስችል ስምምነት ተፈርሟል፡፡

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው መንግስቴ ከቻድ የሲቪል አቪዬሽን ሚኒስቴር ሴክሬታሪ ጄኔራል ማሃማት ሳለህ ዱጋ ጋር በአዲስ አበባ ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸውም የኢትዮጵያ አየር መንገድ በቻድ በሚያደርገው በረራ እየገጠመው ያለውን ችግር መቅረፍ የሚያስችል ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

አቶ ጌታቸው መንግስቴ ኢትዮጵያና ቻድ ረጅም ዓመታት ያስቆጠረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ገለፀው÷ በተለይ በአቪዬሽን ዘርፍ በርካታ ተግባራትን በጋራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡

አየር መንገዱ ወደ ቻድ በሚያደርገው በረራ ከታክስ ነፃ የሚያደርገውን የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት በፈረንጆቹ 2008 መፈራረሙን አስታውሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ የቻድ መንግስት ስምምነቱን ተግባራዊ ባለማድረጉ አየር መንገዱ ታክስ እንዲከፍል ተደጋጋሚ ጫና ሲደረግበት እንደቆየ አስገንዝበዋል፡፡

በቅርቡም የቻድ መንግስት የአየር መንገዱን የባንክ አካውንት ዘግቷል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፡፡

በዛሬው ዕለት የተደረገው ስምምነት ችግሩን በመቅረፍ አየር መንገዱ ያለምንም ችግር በረራውን እንዲቀጥል የሚያስችል መሆኑ አንስተዋል፡፡

በሀገራቱ መካከል ተፈርሞ የቆየውን ስምምነት የሀገሪቱ ሲቪል አቪዬሽን ለፓርላማ አቅርቦ ማፀደቅ ሳይችል በመቅረቱ የተፈጠረ ክፍተት መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

በአሁኑ ወቅትም ጉዳዩ ለፖሊሲ አውጪው አካል ቀርቦ እየታየ እንደሆነ የልዑካን ቡድኑ ማስረዳታቸውን የባለስልጣኑ መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.