የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ማስገባቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሙሉ አቅሙ አገልግሎት መስጠት ያልጀመረው የድሬዳዋ ነፃ የንግድ ቀጣና 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ገቢ ማስገባቱ ተገለጸ፡፡
በነፃ የንግድ ቀጣናው የባለድርሻ አካላት ሚና ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ፎረም በድሬዳዋ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በፎረሙ መንግስት የድሬዳዋን ነፃ የንግድ ቀጣና ወደ ሙሉ አገልግሎት ለማስገባት በሚያስችሉት ጉዳዮች ላይ እየመከረ ነው፡፡
በቀጣይ በዘርፉ የሚካሄዱ ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴዎችን በሚያጠናክረው “የልዩ ኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ አዋጅ” ላይ ባለድርሻ አካላትን ያካተተ ውይይት እንደሚካሄድ ይጠበቃል።
የድሬደዋ ነፃ የንግድ ቀጣና ወደ ሥራ በገባ በአጭር ጊዜ ውስጥ 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በተተኪና በወጭ ምርት ገቢ ማስገባት መቻሉን የኢንዱስትሪ ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈፃሚ አክሊሉ ታደሰ አስታውቀዋል።
ቀጣናው ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ያስችለው ዘንድም አዳዲስ አሰራሮች ቀረፆ በሥራ ላይ እንዲውሉ ሁኔታዎችን አመቻችቷል ብለዋል።
150 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈውን የነፃ ንግድ ቀጣና ዋና መስሪያ ቤት ከ2 ሺህ 300 በላይ የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ነው ያመላከቱት።
48 ሄክታር ላይ ያረፈው የመጋዘን አገልግሎትም የዉሃ፣ መብራት፣ የሥልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተመልክቷል።
በቀጣይም ይህንን አገልግሎት ለማስፋት ያስችል ዘንድ ተጨማሪ 4 ሺህ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱ ተጠቁሟል፡፡
ከ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ካስመዘገቡ ባለሐብቶች ጋር ለመሥራት የሚያስችል ሥምምነት በመፈጸምም አዲሱን ልዩ የኢኮኖሚ ዞን አዋጅ መፅደቅ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ነው የተናገሩት።
የድዳዋ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ከድር ጁሃር በበኩላቸው÷ ነፃ የንግድ ቀጣናው በተጠናከረ መንገድ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድ አስተዳደራዊ ድጋፎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።
የኢትዮ ጅቡቲ ፈጣን መንገድ መሠራት ለነፃ ንግድ ቀጣናው ግንኙነት አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዳለውም ተናግረዋል።
የባቡርና የአውሮፕላን አገልግሎቶችም ምርትን የመላክና መቀበል ሂደቱን ለማፋጠን የሚያስችሉ ሌላኞቹ አማራጮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በኢዮናዳብ አንዱዓለም