Fana: At a Speed of Life!

የአዕምሮ ህሙማንን በሰንሰለት ማሰር ሊታገድ እንደሚገባ ሂዩማን ራይትስ ዎች አሳሰበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሂውማን ራይትስ ዎች የአዕምሮ ህሙማንን በሰንሰለት ማሰር ሊታገድ እንደሚገባ አሳስቧል።

ድርጅቱ የአዕምሮ ህሙማንን አያያዝ አስመልክቶ በጋና ሁለት ማዕከላት ላይ ባደረገው ጥናት፥ ጋና በፈረንጆቹ 2017 የአዕምሮ ጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች በሰንሰለት ማሰር እንዲቆም የጣለችው እገዳ ስራ ላይ አለመዋሉን ገልጿል።

የእዕምሮ ጤና መታዎክ ችግር ያለባቸውን ሰዎች ድጋፍና ክትትል የማግኘት ፣ መኖሪያ ቤት የማግኘት እና ከጥገኝነት ተላቀው የራሳቸውን ኑሮ መኖር እንዲችሉ የስራና ስልጠና ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም ድርጅቱ ያጠናው ጥናት አመላክቷል፡፡

የሀገሪቱ መንግስት ምንም እንኳን በፈረንጆች 2017 የአዕምሮ መታዎክ ችግር ያለባቸውን ሰዎች በሰንሰለት ማሰር በህግ ቢከለክልም የአፈጻጸም ስልቶችን ያካተተ የተግባር ስራ ባለመስራቱ በእየ እምነት ተቋማቱ የአዕምሮ ህሙማን ሰብዊነትን ባልጠበቀ መልኩ ታስረው እንደሚገኙ የድርጅቱ ጥናት ውጤት ያመላክታል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች በፈረንጆች አቆጣጠር ከጥቅምት 19 እስከ 23 ቀን 2023 በጋና ምስራቃዊ ክፍል ሁለት መንፈሳዊ የፈውስ ማዕከላትን በመጎብኘት ከ30 በላይ ለሆኑ ሰዎች ቃለ መጠይቅ ማድረጉን አስታውቋል።

በቃለመጠይቁ የአዕምሮ ጤና መታዎክ ያጋጠማቸውን ሰዎች ፣ የጸሎት ካምፕ ሰራተኞች፣ የአዕምሮ ጤና ላይ የሚሰሩ አካላትን ፣ የአዕምሮ ጤና ባለሙያዎችን እና ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እንደተካተቱ ጠቅሷል፡፡

በዚህም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ በሁለቱ ካምፖች ውስጥ ከፍላጎታቸው ውጪ በሰንሰለት የታሰሩ 10 የአዕምሮ ጤና ህሙማን ላልታወቀ ጊዜ ያህል ለእስራት እና እንግልት መዳረጋቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ይህም የጋና መንግስት የአዕምሮ ጤናን አስመልክቶ በፈረንጆቹ 2017 ያወጣውን ህግ ወደ ተግባር አለመቀየሩን የሚያመላክት ነው ሲሉ በሂዩማን ራይትስ ዎች የአካል ጉዳተኞች መብት ምክትል ዳይሬክተር ኤልዛቤት ካሙንዲያ ገልጸዋል፡፡

ስለሆነም መንግስት የተጣለውን እገዳ ወደ ተግባር በመቀየር የአዕምሮ ህሙማኑ ጤና እንዲሻሻልና ህሙማኑ በተገቢው መልኩ እንዲያዙና ተገቢ የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ ሊያደርግ ይገባልም ነው ያሉት፡፡

ደብረ ኮሬብ የጸሎት ማዕከል በሚባል ቦታ የተመለከተው የሂውማን ራይትስ ጥናት አድራጊ እንደገለጹት÷ በጉብኝታቸው በየክፍሉ የወዳደቁ ሰንሰለቶችን እንዳገኙና በሰንሰለት ታስራ ለሁለት ሳምንት ያህል በባዶ ክፍል የቆየች የ19 ዓመት ወጣትና ለሁለት ወራት ያህል በሰንሰለት ታስሮ የቆየ አንድ የአዕምሮ ታማሚ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ ቦታ ታስረው የተመለከቷቸው የአዕምሮ ህሙማን ስለገጠማቸው የምግብ እጥረት፣ እስርና እንግልት በምሬት እንደሚገልጹ አንዳንዶችም እንደተዳከሙ ለማየት መቻላቸውን የሂውማን ራይትስዎች አጥኚዎች አመላክተዋል፡፡

በአዴሶ በሚገኘው የንፁህ ፓወር ጸሎት ካምፕ ውስጥም አንዲት ሴትን ጨምሮ ዘጠኝ ሰዎች በሰንሰለት ታስረው ማግኘቱንም ነው የገለጸው።

ሂዩማን ራይትስ ዎች በሁለቱም ካምፖች በቂ ምግብ መከልከል፣ ንፅህና እጦት እና የጤና አገልግሎት እጦት፣ የነፃነት እጦት እና የመንቀሳቀስ ነጻነትን ጨምሮ የተለያዩ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመልከቱን ገልጿል፡፡

መንግስት በጸሎት ካምፖች ውስጥ የሚደርሰውን እስራት እና ሌሎች የመብት ጥሰቶችን ለማስቆም አፋጣኝ እርምጃ ሊወስድ ይገባል ሲልም ድርጅቱ አሳስቧል።

የአዕምሮ ህሙማን በነፃነት መኖር እንዲችሉ ከጉዳዩ ጋር የሚሰሩ ድርጅቶች ተገቢው ድጋፍ ሊደረግላቸው እንደሚገባም በጥናቱ ተገልጿል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.