ባለፉት 24 ሰዓታት ለ3 ሺህ 460 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 24 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 12 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) ባለፉት 24 ሰዓታት ለ3 ሺህ 460 ሰዎች የላቦራቶሪ ምርመራ ተደርጎ 24 ሰዎች የኮሮና ቫይረስ እንደተገኘባቸው የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታወቁ።
ከዚህ ውስጥ 18 ወንድ ስድስቱ ደግሞ ሴት ሲሆኑ፥ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው ተብሏል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች እድሜያቸው ከ4 እስከ 58 አመት የሚገኙ መሆናቸውንም ሚኒስተሯ አስታውቀዋል።
ቫይረሱ የተገኘባቸው 9 ከአዲስ አበባ፣ 7 ከትግራይ ክልል እንዲሁም 8 ሰዎች በአማራ ክልል መተማ ለይቶ ማቆያ ያሉ ናቸው።
ከእነዚህ ውስጥ 12ቱ የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ፥ ስምንቱ ደግሞ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ግንኙነት የነበራቸው ናቸው።
እንዲሁም አራት ሰዎች ደግሞ የውጭ ሃገር የጉዞ ታሪክም ሆነ ቫይረሱ ከተገኘበት ሰው ጋር ግንኙነት የሌላቸው መሆኑ ተገልጿል።
ሚኒስትሯ አዲስ ያገገሙ 2 ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው፥ ይህም ከቫይረሱ ያገገሙ ሰዎች ቁጥርን 122 እንዳደረሰው ገልጸዋል።
#FBC
የዜና ሰዓት ሳይጠብቁ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ትኩስ እና ሰበር ዜናዎችን በፍጥነት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት መልክ በስልክዎ ላይ እንዲደርስዎ ወደ 8111 OK ብለው ይላኩ።