ከ620 ሺህ በላይ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶች በኦን ላይን ተሰጠ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር አቀፍ ደረጃ ከሐምሌ እስከ ጥቅምት 15 ቀን 2016 ድረስ 621 ሺህ 437 የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶች በኦን ላይን መሠጠቱን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በሚኒስቴሩ የላይሠንሲንግ እና ሬጉላቶሪ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ጅራታ ነመራ እንደገለጹት÷ አገልግሎቱ በተገልጋዮች ዘንድ ጊዜንና ገንዘብን ከመቆጠቡ ባሻገር ወረፋን እና ሕገ- ወጥ ሠነዶችን አስቀርቷል፡፡
የኦን ላይን አገልግሎቱ ለቅጾችና ተያያዥ ጉዳዮች ይወጣ የነበረን ገንዘብ አስቀርቷል ማለታቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
በ2016 የበጀት ዓመት ከታቀደው 2 ነጥብ 8 ሚሊየን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቶች ውስጥ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ያህሉን በኦን ላይን ለመስጠት መታቀዱንም አመላክተዋል፡፡