Fana: At a Speed of Life!

በሐረሪ ክልል በ356 ሚሊየን ብር ወጪ የውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል በ356 ሚሊየን ብር ወጪ ተጨማሪ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን የክልሉ ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት አስታወቀ።

ከከተማው ጽዳትና ፍሳሽ አወጋገድ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ትኩረት መደረጉ ተመላክቷል።

የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲኒ ረመዳን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ በክልሉ ባለው የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም ምክንያት በአሁኑ ወቅት ለነዋሪው በ15 ቀን አንድ ጊዜ ብቻ ውሃ በፈረቃ እየቀረበ ይገኛል።

ይህንን ችግር ለመቅረፍም በተያዘው ዓመት በ356 ሚሊየን ብር ወጪ አዳዲስ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

ግንባታቸው በመከናወን ላይ ያሉት የውሃ ፕሮጀክቶች በዓመቱ መጨረሻ ለአገልግሎት እንደሚበቁም አቶ ዲኒ አስረድተዋል።

በክልሉ ኤረር አካባቢ እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደር አሶሊሶ ቀበሌ ግንባታቸው እየተከናወነ ያለው 6 አዳዲስ የውሃ ተቋማት ሲሆኑ ቀሪዎቹ በክልሉ ሦስት የገጠር ወረዳዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ግንባታቸው ከ2015 በጀት ዓመት መጨረሻ ጀምሮ እየተከናወነ ያለው የውሃ ተቋማት እስከተያዘው በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ተጠናቀው ለአገልግሎት እንደሚበቁም አስታውቀዋል።

የፕሮጀክቶቹ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ መሆኑንም ሥራ አስኪያጁ አመላክተዋል።

በተጨማሪም÷ በክልሉ 6 ወረዳዎች በ100 ሚሊየን ብር ወጪ 90 የጋራ መጸዳጃ ቤቶች እየተገነቡ ሲሆን የቆሻሻ ፍሳሽ አወጋገድ ለማዘመንም የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.