Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ተከፈተ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የሚወያየውና ውሳኔ የሚሰጠው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ተከፍቷል፡፡

ምልዓተ ጉባኤውን በፀሎት የከፈቱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የቀደምት አባቶቻችንን የሀይማኖት ፅናትና ጥንካሬን የመጠበቅና መድገም ሀላፊነትን ጉባኤው በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።

ቤተክርስቲያኗ ያላትን የሰው ሀይል በቃለ ወንጌል ማነፅ፣ የአስተዳደርና የሀብት አያያዟን በትክክል መጠቀምና መገንባት ላይ እንደምትሰራ ተናግረዋል።

የዕቅበተ ንዋይ፣ የዕቅበተ ሃይማኖት፣ የስልጠናና ትምህርት፣ የገዳማትና ቱሪዝም፣ የምርትና የደን ሀብት፣ የፋይናንስ ሴክተርና የስብከተ ወንጌል ተልእኮ ዘመኑ በሚጠይቀው የአመራርና የአሰራር ጥበብና ስልት እየታገዝን፣ ህዝባችንንም ከጎናችን እያሰለፍን የምንሰራበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ህዝቡ የሚፈልገውን ሰላምና አንድነት ለማምጣት የቤተክርስቲያን ሐይል ትልቁን ድርሻ ይወስዳል ያሉት ፓትርያርኩ፤ ቤተክርስቲያኗ ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ የሰላም ጉዞን እንደምታከናውን ገልፀዋል።

ከዚህ አንጻር ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍንና ቤተክርስቲያኗም አንድነት እንዲረጋገጥ በብርቱ መስራት እንደሚያስፈልግ አንስተዋል፡፡

አኩርፈው የተለዩትን ወደ እኛ እናምጣቸው እኛም ኩርፊያን ከሚያስከትል ድርጊት በመራቅ በአንድነት፣ በእኩልነትና በጋራ ሆነን ታላቋን ቤተክርስቲያን እንሰብስብ፣ እናገልግል፣ እንምራ፣ እንጠብቅ ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በቅድስት አባተ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.