Fana: At a Speed of Life!

ትኩረት የማጣትና ከፍተኛ ያለመረጋጋት ችግር ምንድን ነው?

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 10፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ትኩረት የማጣትና ከፍተኛ ያለመረጋጋት ችግር (Attention deficit hyperactivity disorder) በህክምናው አጠራር “ኤዲኤችዲ” በስሜት የተሞላ ያልተለመደ በከፍተኛ ደረጃ የመቁነጥነጥና ትኩረት የማጣት ባህሪያትን የሚያስከትል የአእምሮ ጤና ችግር ነው።

ለዚህ ችግር የተጋለጡ ሰዎች አንድ ነገር ላይ ትኩረት ለማድረግና በአንድ ቦታ ላይ ለረዥም ጊዜ በትዕግስት ለመቆየት ይቸገራሉ፡፡

ለችግሩ በተጋለጡ ሰዎች ላይ ከፍተኛ የስሜት መዋዠቅና ያለመረጋጋት ችግር በአብዛኛው ጊዜ የሚታይባቸው ሲሆን ይሄም በማህበራዊ ኑሯቸው፣ በስራቸውና በአጠቃላይ እንቅስቃሴያቸው ላይ ችግር ይፈጥርባቸዋል፡፡

“ኤዲኤችዲ” በህጻናትም ሆነ በአዋቂዎች ላይ ሊከሰት የሚችል የአእምሮ ጤና ችግር እንደሆነ የኸልዝ ላይን መረጃ ያመላክታል፡፡

ለኤዲኤችዲ ህመም የተጋለጡ ሰዎች የተለያዩ ምልክቶች የሚያሳዩ ሲሆን ዋና ዋናዎቹ ግን የሚከተሉት ናቸው፡-

• በአንድ ነገር ላይ ትኩረት አድርጎ ለመቆየት መቸገር፣
• የጀመሯቸውን ስራዎች አስታውሶ ያለመጨረስ፣
• በቀላሉ መረበሽ ፣
• በአንድ ቦታ ተረጋግቶ የመቀመጥ ችግር፣
• የሰዎችን ንግግር ወይም ጨዋታ መረበሽ ወይም ማቋረጥ፣

ምልክቶቹ እንደ ህመሙ ደረጃ ሊለያዩ እንደሚችሉም ነው መረጃው የሚያሳየው፡፡

ለ”ኤዲኤችዲ” አጋላጭ ምክንያቶች ምንምን ናቸው?

የህመሙ ምክንያት በትክከክል ምን እንደሆነ ማወቅ እንደማይቻል በበርካታ ጥናቶች ቢገለጽም በነርቭ ችግርና በዘር ሀረግ ምክንያት ሊመጣ እንደሚችል ግን ይታመናል፡፡

መልዕክቶችን ከአንድ ነርቭ ወደ ሌላ ለማንቀሳቀስ የሚያግዘው “ዶፓሚን” የተባለ በአንጎል ውስጥ የሚገኝ ኬሚካል መጠን መቀነስም ለችግሩን እንደሚያመጣ በዘርፉ የተጠኑ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

“ኤዲኤችዲ” ያለበትን ህጻን ወይም አዋቂ በሚያሳየው ምልክት እንጂ በህክምና ወይም በምርመራ ማወቅ የሚቻል ባለመሆኑ እነዚህ ምልክቶች የታየበት ሰው የነርቭ ወይም የስነ አዕምሮ ሃኪም እንዲያየው ይመከራል፡፡

የ”ኤዲኤችዲ” ሕክምና ምንድን ነው?

“ኤዲኤችዲ” የባህሪ፣ ምክርና መድሃኒትን የሚያካትቱ ህክምናዎች አሉት።

ከህክምና በተጨማሪ የአኗኗር ሁኔታን በመቀየር፣ የተመጣጠነ ምግብ በመመገብ፣ ቢያንስ በቀን ውስጥ ለአንድ ሰዓት ያህል አካላዊ እንቅስቃሴ በማድረግና ብዙ እንቅልፍ በመተኛት ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ይገልጻሉ፡፡

በተጨማሪም÷ ህሙማኑ የስልክ፣ የኮምፒውተርና የቴሌቪዝን አጠቃቀማቸው ላይ ገደብ ማስቀመጥ፣ ዮጋ መስራትና ከቤት ውጭ ረዥም ጊዜ ማሳለፍ የተሻለ ውጤት ሊያመጣ ይችላል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.