በሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮረው “የእንቆጳ” ጉባዔ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 1፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሥራ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂና ኢኖቬሽን ላይ ትኩረት ያደረገው “የእንቆጳ” ጉባዔ በአዲስ አበባ ሚሊንየም አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
በጉባኤው መክፈቻ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁንን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
ጉባዔው ኢትዮጵያ በዲጂታል የሥራ ፈጠራ ላይ ያላትን እምቅ አቅም በማስተዋወቅ በዘርፉ የሚፈጠሩ የሥራ ዕድሎችን ለማስፋት ያለመ እንደሆነ መገለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሥራ ፈጣሪዎች ምርትና አገልግሎታቸውን የሚያስተዋውቁበትና የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት ኤግዚቢሽን በጉባዔው ተከፍቷል።
በኤግዚብሽኑ ሥራ ፈጣሪዎች፣ ቴክኖሎጂ አልሚዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ጀማሪ የንግድ ሥራ ባለሙያዎች እንዲሁም የትምህርትና የፋይናንስ ተቋማት እየተሳተፋ ይገኛል።
ለሁለት ቀናት በሚካሄደው ጉባኤ በክህሎት ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄዱም ተጠቁሟል።