ቻይና የእስራዔል – ሐማስን ግጭት ለማስቆም እናሸማግል ስትል ለግብፅ ጥሪ አቀረበች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና የእስራዔል እና የሃማስ ግጭት እጅግ እንዳሳሰባት እና ሀገራቱን ከግብፅ ጋር በመሆን ማሸማገል እንደምትፈልግ ገለጸች፡፡
በቻይና የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ ዣይ ጁን እንዳሉት÷ በተለይ ጦርነቱ በሁለቱ ወገኖች መካከል ከተቀሰቀሰ ጀምሮ እየተቀጠፈ ያለው የንጹሃን ሕይወት እንዳሳሰባቸው ሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ፖስት ዘግቧል፡፡
በመሆኑም ሀገራቱን ከግብፅ ጋር በመሆን ለማሸማገል ፍላጎት እንዳላቸው በግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፍልስጤም ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ለሆኑት ኦሳማ ከድር በሥልክ ነግረዋቸዋል፡፡
በመካከለኛው ምሥራቅ በሚነሱ አለመግባባቶች ውስጥ ቤጂንግ ለየትኛውም ወገን እንደማትወግን መናገራቸውንም መረጃው አመላክቷል፡፡
ከፍልስጤም ጤና ሚኒስቴር ፣ ከፍልስጤም ቀይ ጨረቃ ማኅበር እና ከእስራዔል ጦር ኃይል የተገኙት ጥምር መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ÷ እስከ አሁን ድረስ የ2 ሺህ 173 ሰዎች ሕይወት ከሁለቱ ወገን ተቀጥፏል፡፡
8 ሺህ 137 ሰዎች ደግሞ በጦርነቱ ምክንያት አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ነው የተጠቆመው፡፡