Fana: At a Speed of Life!

በአፍሪካ በሴት ልጅ ግርዛት በዓመት 44 ሺህ ልጃ-ገረዶች ሕይወታቸውን ያጣሉ – ጥናት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 30፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፍሪካ በሴት ልጅ ግርዛት ምክንያት በዓመት 44 ሺህ ያኅል ልጃ-ገረዶች ሕይወታቸውን እንደሚያጡ ጥናት አመላከተ፡፡

ይፋ የሆነው የጥናት ውጤት ትኩረት ያደረገው ኢትዮጵያ ፣ ቤኒን ፣ ቡርኪና ፋሶ ፣ ካሜሩን ፣ ቻድ ፣ ኮት ዲቯር ፣ ግብፅ ፣ ጊኒ ፣ ኬንያ ፣ ማሊ፣ ኒጀር ፣ ናይጄሪያ ፣ ሴኔጋል ፣ ሴራሊዮን እና ታንዛኒያን በጥናቱ አካቶ ነው፡፡

በሀገራቱ በኤች. አይ. ቪ / ኤድስ ፣ ኩፍኝ ፣ ማጅራት-ገትር ፣ በተመጣጠነ የምግብ እጥረት ፣ በአካላዊ አደጋ ፣ በትክትክ እና በመሳሰሉት ከሚሞቱት በላይ በሴት ልጅ ግርዛት ሕይወታቸውን የሚያጡት ሴቶች ቁጥር እንደሚልቅ ‘ኔቸር ሳይንቲፊክ’ ላይ የወጣውን ጥናት ጠቅሶ ኔሽን አፍሪካ ዘግቧል፡፡

በሴት ልጅ ግርዛት ሕይወታቸውን የሚያጡ ሴቶች ቁጥር በ50 በመቶ ማደጉ እንዲሁም ዕድሜያቸው አምሥት ሳይሞላ የሚቀጠፉትም ቁጥር መጨመሩም ተመላክቷል፡፡

ከዚህ ባለፈም በአፍሪካ በተደጋጋሚ ግርዛት የሚፈጸምባቸው ልጃገረዶች እንዳሉና እነዚህም ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እንደሚጋለጡ ተጠቁሟል፡፡

ለአብነትም በግብረ-ሥጋ ግንኙነት ወቅት የማቃጠልን ሥሜት ጨምሮ ውስብስብ ለሆኑ የማሕጸን ችግሮች መዳረግ ፣ ለወሲብ ሥሜት መቀነስ እንዲሁም በልጃገረዶች መካከል የሚፈጠር የአካልና የአዕምሮ ጤና ዕድገት ውስንነት ተጠቅሰዋል።

ጥናቱ ከእንግሊዞቹ ቢርሚንግሃም እና ኤክስተር ዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ ሁለት አጥኚዎች የተሠራ ነው፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.