በአማራ ክልል የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ መንጋ ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል ርጭት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መስከረም 28፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል የተከሰተውን የግሪሳ ወፍ መንጋ ለመከላከል በባሕላዊ ዘዴ የተጀመረው ሥራ በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት በመታገዝ ተጠናክሮ መቀጠሉን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው የሰብል ልማትና ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ አግደው ሞላ÷ የግሪሳ ወፍ መንጋው በሰሜን ሸዋ ዞን ሁለት ወረዳዎች መታየት የጀመረው ካለፈው ነኀሤ ወር 2015 ዓ.ም ጀምሮ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ በሰሜን ሸዋ፣ በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ በደቡብና ሰሜን ወሎ ዞኖች በሚገኙ 14 ወረዳዎች ውስጥ በ58 ቀበሌዎች ተስፋፍቶ መታየቱንም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
የክልሉ ግብርና ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር መንጋው ያለባቸውንና የሚያድርባቸውን ቦታዎች በመለየት በአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ሥራ እየተካሄደ ነው ተብሏል፡፡
ለአብነትም በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ዳዋጨፋና ጅሌ ወረዳዎች በተለዩ የግሪሳ ወፍ መንጋ የማደሪያ ቦታዎች የርጭት ሥራ መካሄዱን ጠቅሰው÷ በደቡብ ወሎ ቃሉ ወረዳም የኬሚካል ርጭት ሥራው መካሄዱን ተናግረዋል።