Fana: At a Speed of Life!

በኮምቦልቻ ጊዜያዊ ማቆያ የነበሩ ተጠርጣሪዎች የተሃድሶ ስልጠና አጠናቀው ህብረተሰቡን ተቀላቀሉ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 27፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ኮምቦልቻ ጮሪሳ ጊዜያዊ ማቆያ የነበሩ ተጠርጣሪዎች የተሃድሶ ስልጠና አጠናቀው ህብረተሰቡን ተቀላቀሉ።

ተጠርጣሪዎች በተሃድሶ ስልጠናው ጥሩ ግንዛቤ ማግኘታቸውን ጠቅሰው ፥ በቀጣይ በሀገራዊ የልማትና የሰላም ግንባታ የድርሻቸውን ለመወጣት ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡

በጮሪሳ ቆይታቸው በፌዴራል ፖሊስ ለተደረገላቸው መልካም አያያዝ አመስግነው ፥ ለምርቃት በመብቃታቸውም መደሰታቸውንም ነው የገለጹት።

የተሃድሶ ስልጠና ወስደው የተመረቁት ተጠርጣሪዎች በህብረተሰቡ ውስጥ ግንባር ቀደም የሰላም አምባሳደርና የልማት ተዋናይ ለመሆን መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

በቀጣይ በሚከናወኑ ሀገራዊ የልማት ስራዎችና የሰላም ግንባታ ሂደቶች የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውንም ነው ያረጋገጡት።

የሰላም ጉዳይ የጋራ ሃላፊነነት በመሆኑ ሁላችንም የሰላም ዘብ በመሆን ለተግባራዊነቱ በጋራ እንሰራለን ሲሉም ገልጸዋል።

በምረቃ መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሊ መኮንን ፥ የተሃድሶ ስልጠና ወስደው የተመረቁ ተጠርጣሪዎች በሄዱበት ሁሉ የሰላም አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ አሳስበዋል።

ህብረተሰቡ ወንጀለኞችን በማጋለጥ በህግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም መጠየቃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ሳሙኤል ሞላልኝ በበኩላቸው ÷ የችግሮች ሁሉ መፍቻ መንገድ ሰላማዊ ውይይት ብቻ መሆኑን ገልጸው ፤ በጥፋት መንገድ የሚጓዙ አካላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

የተሃዲሶ ስልጠና ወስደው የተመረቁት ተጠርጣሪዎች የሰላምና ጸጥታ አጋር ሆነው በተግባር ሊያሳዩ ይገባል ያሉት ደግሞ የምስራቅ አማራ ኮማንድ ፖስት ምክትል ሰብሳቢ ሜጀር ጀነራል ሻምበል ፈረደ ናቸው ።

የተሃድሶ ስልጠና ተመራቂዎች በየደረጃው ካለው የጸጥታ ሃይል ጋር በመተባበር ለሀገርና ለህዝብ ሰላምና ደህንነት እንዲሰሩም አሳስበዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.