Fana: At a Speed of Life!

የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ሕብረት ጉባዔ የአጋሮችን ትስስርና ትብብር የፈጠረ ነው – በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የዓለምአቀፉ የቴሌኮም ሕብረት ጉባዔ የአጋሮችን ትስስር፣ ትውውቅና ትብብር የፈጠረ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ከመስከረም 22- 24 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው የዓለም አቀፉ የቴሌኮም ሕብረት የአፍሪካ ሀገራት ጉባዔ በስኬት ተጠናቋል።

በጉባዔው ማጠቃለያ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) እንዳሉት ÷መድረኩ የአፍሪካን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እድገት ዘላቂነት ያለው የቴሌኮም እድገትን በማፋጠን እንዴት መጠቀም እንደሚቻል መዳሰስ አስችሏል ።

በዘርፉ ጠቀሜታ እና ቀጣይ አስቻይ አቅም ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መምከር በመቻሉ ጠቃሚ ውይይት ተካሂዷልም ነው ያሉት፡፡

በተለይም በራስ አቅም ችግር ፈች መፍትሄዎች ላይ አተኩረው የተነሱ ጉዳዮች መሰል መድረኮችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ልምድ ከማስገኘቱም በላይ ተሳታፊ ሀገራት የዲጂታል ክፍፍልን ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ፣ ፈጠራን ለማበረታታት የሚያስችሉ ደንቦችን ለማውጣት ፣ ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ የሚያስችሉ ግብዓቶችም ተገኝተውበታል ብለዋል።

ከወጣቶች፣ ከሥራ ፈጣሪዎች፣ ከግሉ ዘርፍ እንዲሁም ከመንግሥት ተወካዮች የተገኙ ግብዓቶችን ምቹ ዕድሎችን በማጎልበት ያጋጠሙ መሰናክሎችን ለመፍታት ሁሉም ተባብሮ ሊጠቀምባቸውና ስራ ላይ ሊያውላቸው እንደሚገባም አንስተዋል፡፡

ዲጂታል ፈጠራን በመጠቀም ምቹ የስራ ፈጠራ ስነ-ምህዳርን ለማጠናከርና የዳበረ ዲጂታል ኢኮኖሚ ለመገንባት ልናውለው ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ለዚህም ተደራሽና ተመጣጣኝ የብሮድባንድ ግንኙነቶችን መዘርጋትና የተጠቃሚነት ክህሎት ላይ በትኩረት መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

መንግስታት፣ የዘርፉ ተቆጣጣሪዎች እና የግሉ ሴክተር ተዋናዮች ለስነ-ምህዳሩ መፈጠር በትብብር ሚናቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡

ጉባዔው የአጋሮችን ትስስር፣ ትውውቅና ትብብር የፈጠሩ ግንኙነቶች የፈጠረ እና የጋራ ቃል ኪዳኖች የታደሱበት እንደነበርም ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.