Fana: At a Speed of Life!

በአቃቂ ቃሊቲ የውሃ ማሞቂያ ፈንድቶ የ3 ሰዎች ህይወት አለፈ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 የውሃ ማሞቂያ ፈንድቶ የሦስት ሰዎች ሕይዎት ማለፉ ተሰማ፡፡

የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሞያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለፋና ብርድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት ፥ አደጋው የደረሰው ዛሬ ከቀኑ 10:35 ነው፡፡

አደጋው በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 የቀድሞ አቃቂ ጨረቃ ጨርቅ ጊቢ ውስጥ በሚገኝ ሶሻል ሳሙናና ፕላስቲክ ፋብሪካ

ውስጥ በተፈጠረ የውሃ ማሞቂያ ፍንዳታ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

በዚህም ህይዎታቸው ካለፉት ሦስት ሰዎች በተጨማሪ ለጊዜዉ ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋልም ነው የተባለው፡፡

በአደጋው ህይወታቸዉ ያለፉትና ጉዳት የደረሰባቸዉ ሰዎች የፋብሪካዉ ሰራተኞች ሲሆኑ ፥ ተጎጂዎች ወደ ህክምና ተቋም መወሰዳቸውን አቶ ንጋቱ ማሞ ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ዛሬ ከቀኑ 6:17 ላይ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 መሿለኪያ ጤና ጣቢያ አካባቢ በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ የተነሳ የእሳት አደጋ በንብረት ላይ ጉዳት አድርሷል።

የእሳት አደጋዉ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት ተለኩሶ በተረሳ ሻማ ምክንያት የደረሰ ሲሆን ፥ በአደጋዉ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን የሚገመት ንብረት ወድሟል።

አደጋዉን ለመቆጣጠር አራት የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪ ና 29 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች መሰማራታቸውን አቶ ንጋቱ ማሞ ተናግረዋል ፡፡

አደጋዉን ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረትም በአቅራቢያው ባሉ ህንጻዎች ሳይዛመት በቁጥጥር ስር ማዋል የተቻለ ሲሆን ፥ በዚህ ሂደት 150 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት ማዳን መቻሉ ተገልጿል።

በትዕግሥት ስለሺ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.