Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውኅሎት የተደገፈ ዲጂታል “ስቴትስኮፕ”ን በመጠቀም በአፍሪካ 2ኛዋ ሀገር ሆነች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 22፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰው ሠራሽ አስተውኅሎት (አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ) ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዲጂታል “ስቴትስኮፕ” በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆኗል፡፡

አዲሱ ዲጂታል ስቴትስኮፕን ለሕክምና ባለሙያዎች የማስተዋወቅ ሥነ – ሥርዓት በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ተካሂዷል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱራዛቅ አሕመድ በሥነ – ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት÷ የቴክኖሎጂው ወደ ሀገር ውስጥ መግባት የመጀመሪያው ዲጂታል “ስቴትስኮፕ”ን የሚጠቀም ሆስፒታል አድርጎታል፡፡

ኢትዮጵያ በሰው ሠራሽ አስተውኅሎት ቴክኖሎጂ የተደገፈ ዲጂታል “ስቴትስኮፕ”ን በመጠቀም ከደቡብ አፍሪካ ቀጥላ ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ሀገር ናት ማለታቸውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሣይንስ ኮሌጅ መረጃ ያመላክታል፡፡

ዲጂታል “ስቴትስኮፕ” ከዚህ ቀደም ከተለመዱት የምርመራ መሳሪያዎች በተለየ ጥራት ያለውን መረጃ ከነውጤቱ የሚገልጽ ቴክኖሎጂ መሆኑንም ነው ያስገነዘቡት፡፡

በተጨማሪም ታማሚው ካለበት ቦታ ለሐኪሙ መረጃዎችን በቀላሉ ለማድረስ ያስችላል ነው ያሉት፡፡

ቴክኖሎጂው የተሻለ ጥራት ያለው ሕክምና ለመስጠት ጥቅሙ የጎላ መሆኑን አንስተው÷ ቴክኖሎጂው በኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ እንዲውል የደቡብ ኮሪያ ባለሙያዎችና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ላደረጉት ጥረት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.