የኢሬቻ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ መሰከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ ሳምንት የመክፈቻ መርሐ-ግብር በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው።
በመርሐ-ግብሩ በአሉን የሚያስተዋውቁ የግጥም ፣ የፋሽን ሾው ፕሮግራሞችን ጨምሮ ባህላዊ ጭፈራዎችም ቀርበዋል።
መርሐ-ግብሩ የኢሬቻን እሴቶች ለማስተዋወቅ ያለመ ሲሆን÷ በአሉ በአንድነትና በወንድማማችነት እንደሚከበር ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ በብዝሃ ማንነት የደመቀች በብዙ ባህላዊ እሴቶች የተሸመነች ውብ ሀገር ናት።
ባህል የአንድ ማህበረሰብ ማንነት መገለጫ መሆኑን ገልጸው÷ በከተማዋ የሚከበሩ በአላት የመዲናዋ ድምቀቶች እና ጸጋዎች መሆናቸውን አንስተዋል።
የኢሬቻ በአል ፍቅር ከፍ የሚልበት ግለኝነት ቦታ የሚያጣበት መሆኑን ያነሱት ሃላፊዋ÷ የገዳ ስርዓት አካል የሆነው ይህ በአል የሰላም እና የአንድነት በአል መሆኑን ተናግረዋል።
የአደባባይ በአላት ለቱሪዝም ዘርፍ እድገት ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ ማንሳታቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡