ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ሕብረት አህጉራዊ ጉባኤውን ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ ያካሄዳል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ)ዓለም አቀፉ የቴሌኮም ሕብረት (ITU) የአፍሪካ አህጉራዊ ጉባኤውን ከነገ ጀምሮ በአዲስ አበባ እንደሚያካሂድ ተገለፀ፡፡
ጉባኤው ከነገ ጀምሮ እስከ መስከረም 24 ቀን 2016ዓ.ም እንደሚካሄድም ነው የተገለፀው፡፡
ሕብረቱ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ጋር ያዘጋጁት ጉባኤ ” ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለዘላቂና ፍትሐዊ መጻኢ ጊዜ የአፍሪካ የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራን ማፋጠን” በሚል መሪ ሀሳብ ነው የሚካሄደው።
ጉባኤው በአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን ለማምጣትና የዘላቂ ልማት ግቦችን ማሳካት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክር ኢዜአ ዘግቧል።
የአፍሪካ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ለአህጉሪቷ መጻኢና ዘላቂ የዲጂታል እድገት እንዲሁም ለዓለም አቀፍና አህጉራዊ የልማት ግቦች መሳካት ያለው ሚና ላይ ምክክር እንደሚደረግም ተገልጿል።