Fana: At a Speed of Life!

በዓላት በሰላም እንዲከበሩ ዝግጅት ተደርጓል – ኮማንድ ፖስቱ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 15፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የግሸን ደብረ ከርቤ ንግስ፣ የመውሊድና የመስቀል በዓላት በሰላማዊ መንገድ እንዲከበሩ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን የደቡብ ወሎ ዞንና የደሴ ከተማ አስተዳደር ኮማንድ ፖስት አስታወቀ፡፡

የኮማንድ ፖስቱ አባል ሻለቃ ደግሰው ዶሻ እንደገለጹት÷ መስከረም 21 የሚከበረውን የግሸን ደብረ ከረቤ የንግስ በዓል በሰላም እንዲከበር ማህበረሰቡን በማሳተፍ ተገቢው ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል።

ምዕመናኑ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በዓሉን ያለ ስጋት ማክበር እንደሚችሉም አረጋግጠዋል።

ህብረተሰቡ ለሰላም ባለው ብርቱ ፍላጎትና ትብብር አካባቢውን ሰላም ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይህንን ዘላቂ ለማድረግ በቅንጅት እንሰራለን ብለዋል፡፡

የመውሊድ፣ የመስቀልና ደመራ በዓላትም እንዲሁ በሰላም እንዲከበሩ ተገቢውን ስምሪት በመስጠት ቅደመ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

በዓላቱ በሰላምና በአንድነት እንዲከበሩ የጸጥታ መዋቅሩ ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ ቅደመ ዝግጅት አድርጓል ያሉት ሌላው የኮማንድ ፖስቱ አባል ሻለቃ መላኩ ቶላ ናቸው፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን የመንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ እያሱ ዮሐንስ በበኩላቸው÷ የግሸን ደብረ ከርቤ የንግስ በዓልን ለማክበር ወደ ስፍራው የሚመጡ እንግዶችን በተገቢው ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

በዓሉን ምክንያት በማድረግ አካባቢውን የቱሪስት መዳረሻ ጭምር በማድረግ ለገቢ ምንጭነት እንዲውልም እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የትራንስፖርት ችግር እንዳይኖር ከአጎራባች ዞኖችና ከተሞች ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.