Fana: At a Speed of Life!

የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ኮሚቴ ተዋቅሮ በቅንጅት እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 12፣ 2016 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር ኮሚቴ ተዋቅሮ ሁለን አቀፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው ኃላፊ ኃይሉ አዱኛ÷ ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱ በሰላም በመጠናቀቁ ሁሉን ነገር ለፈጠረ ዋቃ (አምላክ) ምስጋና የሚያቀርብበትና መጪው ዘመን መልካም እንዲሆን ፈጣሪን የሚለምንበት በዓል ነው ብለዋል፡፡

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል “ኢሬቻ የአንድነት እና የወንድማማችነት አርማ” በሚል መሪ ሐሳብ እንደሚከበር ተናግረዋል፡፡

በዓሉ ሰላም፣ ይቅርታና ወንድማማችነትን እንዲሁም የኦሮሞ እሴቶችን በሚያጎለብት መልኩ እንደሚከበር አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የኢሬቻ በዓል እሴቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበርም ከክልል እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ኮሚቴ ተዋቅሮ ሁሉን አቀፍ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡

የጸጥታ አካላት፣ የመገናኛ ብዙሃን፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የበዓሉ ተሳታፊዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በዓሉ በሰላም እንዲከበር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም ጠይቀዋል፡፡

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ኃላፊ ብርሃኑ ጉቴ በበኩላቸው÷ የኢሬቻ በዓል የምስጋና፣ የፍቅር፣ የሰላም፣ የአንድነት እና የይቅርታ በዓል መሆኑን አውስተዋል፡፡

በዓሉ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር ቱሪስቶች ተመራጭ መዳረሻ እንዲሆን በትብብር እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

በቀጣይ ኢሬቻን በዩኔስኮ ለማስመዝገብም የበዓሉን ትክክለኛ የአከባበር እሴት እና ትውፊት ጠብቆ ማክበር እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.