Fana: At a Speed of Life!

የህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለትውልድ አሻራ ማስቀመጥ እንደሚቻል ማሳያ ነው – ምሁራን

አዲስ አበባ ፣ ጳጉሜን 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ ፈተናዎችን ተቋቁሞ ለትውልድ የሚሸጋገር አሻራ ማስቀመጥ እንደሚቻል ትምህርት የሰጠ መሆኑን ምሁራን ገለጹ፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ 4ኛ ዙር የውኃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አብስረዋል።

የውሃ ሙሌቱን ተከትሎ ምሁራን በሰጡት አስተያየት እንደሚሉት÷ የኢትዮጵያዊያን የጋራ ፕሮጀክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እዚህ ደረጃ መድረስ የጋራ ጥረት ውጤት ነው።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) ዓባይ የኢትዮጵያ ማንነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ደግሞ የዛሬው ትውልድ አሻራ የነገው ትውልድ ገጸበረከት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት እንዳላት ገልጸው÷ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ ከዓባይ ጋር ያላትን ትስስር የሚያጸና መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኮተቤ ትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ብርኃነመስቀል ጠና (ዶ/ር) በበኩላቸው ÷ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የሚነጋገሩበት የጋራ ቋንቋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

የግድቡ 4ኛ ዙር ሙሌት ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥም ሆና ማንኛውንም ፕሮጀክት ማሳካት እንደምትችል በግልጽ ያሳየ ነው ብለዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድህነትን በማሸነፍ ለመጭው ትውልድ ብልጽግናን የምናወርስበት የአንድነታችን አርማ፤ የማሸነፋችን ምልክት ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር ብዙ ፈተናዎችን ተቋቁመን በዚህ ልክ መለወጥ ከቻልን ሰላማችንን በጋራ ብናረጋግጥ የት እንደርስ ነበር የሚለውን መላው ኢትዮጵያዊ ቆም ብሎ ሊያየው ይገባል ነው ያሉት።

ትናንት ያጋጠሙንን ፈተናዎች በድል ተሻግረን እዚህ ደርሰናል፤ የዛሬ ፈተናዎችንም አልፈን የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን እንደምናደርግ ያለፍንበት መንገድ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከልመና የምንወጣበት ድህነትን የምናሸንፍበት ፕሮጀክት በመሆኑ መላ ኢትዮጵያዊያን ለግንባታው መጠናቀቅ ጥረታቸውን አጠናክረው መቀጠል ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር) ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ አልፎ አገራትን የሚያስተሳስር በጋራ የመልማት ማሳያ እንደሆነ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላትን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በጋራ የመጠቀም ፍላጎት የሚያንጸባርቅ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.