የመረጃ ጠላፊዎች የቪዲዮ ኮንፍረንስ ፕላትፎርም ‘ዙም’ በማስመሰል ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለመመዝበር እየተጠቀሙበት ነዉ – ጥናት
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 4፣2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የመረጃ መንታፊዎች የቪዲዮ ኮንፈረንስ ፕላትፎርም የሆነዉን ዙም /Zoom/ በማስመሰል የማይክሮሶፍት ተጠቃሚዎችን ሚስጥራዊ መረጃ ለመመንተፍ እየተጠቀሙበት መሆኑን ጥናት ይፋ አድርጓል።
አብኖርማል ሴኪዩሪቲ ይፋ ያደረገዉ መረጃ እንደጠቆመዉ የዙም ተጠቃሚዎች በሃሰተኛ እና ተንኮል-አዘል አገናኞችን በያዙ ኢ-ሜይሎች ኢላማ መሆናቸዉን ጠቅሷል።
ከመረጃ መንታፊዎቹ የሚላኩ የማሳወቂያ መልእክቶች ከዙም የመጣ የስብሰባ ተሳታፉ ማሳወቂያ የሚያስመስልና አታላይ የኢ-ሜይል መልእክቶቹ ከትክክለኛዉ ማሳወቂያ ጋር የተመሳሰሉ ናቸውም ነው ያለው፡፡
በኢ-ሜይል ማስመሰሎች ራስ-ሰር የሆኑ የማሳወቂያ አማራጮችን የሚጠቀሙ መሆኑንም ጠቁሟል።
ከዚያም ባለፈ ተጠቃሚዎች በቅርቡ የተጋበዙት ስብሰባ እንዳመለጣቸዉ በመጥቀስ ያመለጣቸዉን ስብሰባ ቅጂ ለማግኘትም አገናኞች/ links/ እንዲከፍቱ እና ዝርዝር እንዲመለከቱ በመገፋፋት ለሳይበር ጥቃት እንደሚያጋልጧቸዉም ነው ጥናቱ ይፋ ያደረገው።
አክሎም ተጠቃሚው ህጋዊ የሚመስል የቪዲዮ ኮንፈረንስ ፕላትፎርም የሆነዉን የዙም /Zoom/አገናኝን በሚከፍቱበት ጊዜም ወደ ሀሰት የማይክሮሶፍት መግቢያ ገጽ እንደሚወስዱ ታውቋል።
የመረጃ መንታፊዎች ይህን የማታለያ አማራጭን መጠቀም የፈለጉበት ምክንያት የማይክሮሶፍት ተጠቃሚዎችን ሚስጥራዊ መረጃ ለመበርበር እንዲረዳቸዉ እንደሆነ ተመራማሪዎቹ ጠቅሰዋል።
ተጠቃሚዎችም በዙም የሚያደርጉት ስብሰባዎች ላይ ጥንቃቄዎችን ማድረግ የሚገባቸዉ ሲሆን ከማያውቁት አካል የሚላኩ የስብሰባ ተሳተፉ ማሳወቂያ እና ግብዣ ትክክለኛነት ሳያረጋግጡ ከመክፈት ሊቆጠቡ ይገባል ማለቱን ከኢመደኤ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!