Fana: At a Speed of Life!

በጋምቤላ ተከስቶ በነበረው የፀጥታ መደፍረስ የተሳተፉ አካላት በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋምቤላ ክልል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር የተሳተፉ አካላት በህግ እንዲጠየቁ የማድረጉ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለፁ።

በክልሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት ህዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ ባለ ስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በኮንፈረንሱ ማጠናቀቂያ ላይ እንዳሉት÷ በክልሉ ህዝቦች መካከል ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከርና ሰላምን በዘላቂነት ለማስቀጠል ይሰራል ።

በክልሉ የሚታዩትን አለመግባባቶች በውይይት በመፍታት ሰላምን ለማምጣት ሁሉም አንድነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ ገልፀዋል።

በክልሉ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ መበራከት ለግጭቱ መባባስ ምክንያት እንደነበር አንስተው÷ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ የያዙ ግለሰቦች በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመንግሥት ገቢ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

በክልሉ ያለውን ሠላም በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ህዝባዊ የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባልም ብለዋል ርዕሰ መስተዳደሩ፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ባወጡት የአቋም መግለጫ ÷ ሠላም የሁሉም ነገር መሠረት በመሆኑ የተጀመረው ሠላማዊ ውይይት እንዲጠናከር የሚጠበቅባቸውን እንደሚወጡ መናገራቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.