Fana: At a Speed of Life!

ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጠናከረ ቁጥጥር እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከበአል ጋር ተያይዞ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጠናከረ ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ መሆኑን የኢትዮጵያ ምግብና መድሃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።

የ2016 ዓ.ም የዘመን መለወጫ በዓል ግብይት ላይ የወንጀል ተግባራት የሚፈጽሙ ግለሰቦችን በመከታተልና በመቆጣጠር በህግ ተጠያቂ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ባለስልጣኑ አስታውቋል።

የባለስልጣኑ የምግብ አምራች ተቋማት ተቆጣጣሪ አየነው አንዳርጌ እንደገለጹት÷ ለበዓል ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን ጥራትና ደህንነት ለማረጋገጥ የተጠናከረ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እየተከናወነ ነው።

በብዛት ግብይት በሚካሄድባቸውና ምርት በሚመረትባቸው አካባቢዎች ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የጥራት ቁጥጥር በመደረግ ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በምግብና ምግብ ነክ ምርቶች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ስራው በቅንጅት እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ህብረተሰቡ የሚሸምታቸውን ምርቶች በጥንቃቄ ሊያይ ይገባል ያሉት አቶ አየነው÷ በተለይም በየአካባቢው ለገበያ በሚቀርቡ የኢንዱስትሪ ምርቶች የመጠቀሚያ ጊዜያቸውን በጥንቃቄ በማየት መግዛት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በግብይት ወቅት አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙም በባለስልጣኑ ነፃ የስልክ መስመር 8482 ማሳወቅ ወይም ለጸጥታ አካላት መረጃ መስጠት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.