Fana: At a Speed of Life!

በወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት 56 ሚሊየን ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በ2015 በጀት ዓመት በወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ56 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ ተግባራት መከናወናቸውን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር  ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)÷ በበጀት ዓመቱ ሴቶች፣ ህጻናት፣ ወጣቶች፣ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ ስራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።

በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ተቋማቸው የስነ-ልቦና ህክምና፣ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የመልሶ ማቋቋም ተግባራት እንደተከናወኑም አንስተዋል።

በተለያዩ ሱሶች ተይዘው የነበሩ ወጣቶችን ወደ ሰብዕና ግንባታ ማዕከላት በማስግባት አስፈላጊውን ስልጠናና ህክምና በመስጠት ጤናማና አምራች ሃይል እንዲሆኑ መደረጉን ገልጸዋል።

በወሰን ተሻጋሪ የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ከ20 ሚሊየን በላይ ወጣቶችን በማሳተፍ ከ17 ቢሊየን ብር በላይ የሚገመቱ ማህበረሰባዊ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

ሴቶች በፖለቲካው ዘርፍ ያላቸውን ተሳትፎና የውሳኔ ሰጪነት ሚና ለማሳደግም ከ10 ሺህ በላይ ሴቶችን የማብቃት ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።

በዚህም በመላ ሀገሪቱ ባሉ መካከለኛና ከፍተኛ የመንግስት መዋቅሮች 2 ሺህ 500 ሴቶችን በአመራርነት እንዲመደቡ መደረጉን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ህገ-ወጥ ስደትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሁሉም ክልሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ ተሰርቷል።

ከዚህም ባለፈ ህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ይፈፀምባቸዋል ተብለው በሚታሰቡና በጥናት በተለዩ ቦታዎች ላይ ሰፊ ቁጥጥር እየተደረገ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም 158 ህገ-ወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ ደላሎች በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው በህግ እየታየ እንደሚገኝም አንስተዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.