በትግራይ ክልል የተከሰተውን የአምበጣ መንጋ ለመከላከል የተቋቋመው ግብረ-ሃይል ስራ ጀምሯል
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 7፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በትግራይ ክልል የተከሰተውን የአምበጣ መንጋ ለመከላከል በክልል ደረጃ ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ-መስተዳድር ጌታቸው ረዳ አስታወቁ።
ህብረተሰቡ በሰብልና ደን ላይ የተከሰተውን የአምበጣ መንጋ በመከላከል ሂደት ተሷትፎውን አጠናክሮ እንዲቀጥልም አሳስበዋል።
አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት÷ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች በሚባል ደረጃ የአምበጣ መንጋ ተከስቷል።
መንጋው አሁን ላይ በመኸር ሰብልና በደኖች ላይ በመስፈር ጉዳት እያደረሰ መሆኑን ጠቁመው÷ ህብረተሰቡ በየአካባቢው በባህላዊ ዘዴ መንጋውን እየተከላከለ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአምበጣ መንጋው ከአቅም በላይ እየሆነ በመምጣቱ በክልል ደረጃ ግብረ-ሃይል ተቋቁሞ የመከላከል ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል።
የአምበጣ መንጋውን ከምንጩ መከላከል የሚያስችል የኬሚካልና የአውሮፕላን ድጋፍ ከፌዴራል መንግስት እንዲደረግ ስራዎች መጀመራቸውን አቶ ጌታቸው መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡