አብን ሀገሪቱ ለገባችበት ፖለቲካዊ ቀውስ አዲስ የሽግግር መንግሥት መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌለው ገለፀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 29፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሀገሪቱ ለገባችበት ፖለቲካዊ ቀውስ አዲስ የሽግግር መንግሥት መፍትሄ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌለው ገለፀ።
የአብን ብሔራዊ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ ባወጣው መግለጫ፥ ፓርቲው የሀገርን ሉዓላዊነት፣ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት፣ የሕግን የበላይነት በማስከበር ረገድ ኃላፊነቱን በብቃት የሚወጣ አካል እንዲኖር ከማስቻል አንፃር፤ አዲስ የሽግግር መንግሥት መፍጠር በአገሪቱ ከሚታየው ወቅታዊ የፖለቲካና የኃይል አሰላለፍ አውድ አንፃር ሊሳካ የማይችል ሀሳብ ነው ሲልም ገልጿል።
ስለሆነም ምርጫው እስኪካሄድ ድረስ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት መቆየትና የሽግግር ሂደቱን መምራት ለሕዝባችንና አገራችን ሰላምና ደህንነት ካሉት አማራጮች በአንፃራዊነት የተሻለው ነው የሚል አቋሙንም አሳውቋል።
የአማራ ሕዝብና የሌሎች ወንድም ህዝቦች መሰረታዊ ጥያቄዎች ስርዓታዊና መዋቅራዊ በመሆናቸው በዋነኝነት የሚፈቱት በልሂቃን መካከል በሚደረግ ውይይትና ድርድር ከሚመነጭ ፖለቲካዊ መፍትሄ መሆኑን ያምናል ያለው ፓርቲው፥ ብሔራዊ ፖለቲካችን ከጥሬ የስልጣን ትግል ወደ ዘላቂ ሰላም እንዲሻገር ከታሰበ ከአጭር ፖለቲካዊ ትርፍ ይልቅ ዘላቂ የአገርና የሕዝብ ጥቅምን ያማከለና አዲስ ቅርፅና አቅጣጫ ያለው ሰፊና የማያቋርጥ የድርድርና እርቅ ሂደት ያስፈልጋል ብሏል።
ለዚህም ተፎካካሪ ፓርቲዎችን፣ ሲቪክ ማህበራትንና ሌሎችንም ባለድርሻ አካላትን ያካተተና ለሕዝብ ተወካዮች ተጠሪ የሆነ የብሔራዊ ውይይት ኮሚሽን እንዲቋቋም ጠይቋል።
የዜጎችን ሰብዓዊ መብቶች ማስከበር ከመንግሥት ግንባር ቀደም ኃላፊነቶች መካከል መሆኑን በመገንዘብ፤ ሀገሪቱ ባለችበት የስጋት ሁኔታ የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የተለየ ዝግጁነት እንዲደረግ አበክሮ ጠይቋል፡፡
አብን በሕዝባችን ትግል የተሸነፉ ሀይሎች ሀገርን ለማተራመስና እንደገና የጭቆና መንበራቸውን ለመመለስ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ አጥብቆ እንደሚታገለው ያረጋግጣልም ነው ያለው።
ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!