የጋምቤላ ክልል ወቅታዊ የአማራ ክልላዊ መንግሥት የፀጥታ ሁኔታን አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ
በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግሥታችን ኢትዮጵያን በአጭር ጊዜ ውስጥ አፍሪካዊት የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
ለዚህም እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶቻችንን ከሰው ሃይላችን ጋር በማሰናሰል የተጀመሩ ሜጋ ፕሮጄክቶችን በወቅቱ በማጠናቀቅ፤ ሌሎችንም በአስገራሚ ሁኔታ በመጀመር ላይ ይገኛል፡፡
ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና ስጋት የገባቸው ሃይሎች ዕቅዶቻችን እንዳይሳኩ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ መሆናቸው ከእስካሁኑ ተሞክሮአችን ብዙ ማየት ችለናል፡፡
በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ተፈጥሮ የነበረውን ግጭት አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊ መፍትሄ፣ ብሂል መፍታታችን ያልተዋጠላቸው እና የተራዘመ ጦርነት ውስጥ አቆይተውን ከውድቀታችን ለማትረፍ ለሚሹ ሃይሎች እረፍት እንደማይሰጣቸው እናምናለን፡፡
ለዚህም በየጊዜው የተለያዩ አጀንዳዎች እየሰጡን ከችግር አዙሪት እንዳንወጣ እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
ውጪ በሚኖሩ ፅንፈኛ ዩቲውበሮችና አክቲቪስቶች እየተነዱ በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በፋኖ ስም የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛ ዘራፊ ቡድኖች የሕዝብ አግልግሎት መስጫ ተቋማት አገልግሎት እንዳይሰጡ ከማስተጓጎል ባሻገር በአንዳንድ አካባቢዎች በአንጡራ የህዝብ ሃብት የተገነቡ ተቋማትን በማውደምና በመዝረፍ ትውልድ ይቅር የማይለው በደል በማድረስ ላይ ይገኛል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የኩራታችን ምንጭና የሉዓላዊነታችን መገለጫ የሆነው የመከላከያ ሰራዊታችንን እስከ መተንኮስ የደረሰ የክህደት ተግባር በመፈጸም ላይ ይገኛል።
ይህ ሀይል የአማራ ክልል ሕዝብን ለማሰቃየት የተፈጠረ ኃይል እንጂ የአማራ ክልል ወኪል አለመሆኑን በውል በመገንዘብ፣ በቅርቡ በክልሉ ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌዴራል መንግሥት አስፈላጊውን የሕግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጥያቄን ተከትሎ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በክልሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲተገበር በሙሉ ድምፅ አጽድቆ ወደ ሥራ መግባቱን የጋምቤላ ህ/ብ/ክ/መንግሥት በአንክሮ እየተከታተለው ይገኛል፡፡
በመሆኑም ክልሉ ከጦርነት ጉዳት ወጥቶ ሳያገግም ይሄ ችግር በመድረሱ የተሰማንን ሃዘን እየገለጽን፤ በአሁኗ ኢትዮጵያችን ሁኔታ በትጥቅ ትግል የሚመለስ ጥያቄ አለመኖሩ፤ ለዚህም መንግሥት የትኛውም ጥያቄ ቢኖር በሰላም መፈታት እንዳለበት በጽኑ የሚያምን መሆኑ እየታወቀ በጉልበት ፍላጎትን በሌላው ላይ ለመጫን የሚደረግ ሩጫ የትም እንደማያደርስ በውል ሊታወቅ ይገባል እንላለን፡፡
በሌላም በኩል የአማራ ክልል ሕዝብ መብቶችና ጥቅሞች ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጥቅሞች ጋር የተያያዙ መሆናቸውን በውል በመረዳት ከክልሉ መንግሥትና ሕዝብ ጋር ሆነን ይሄንን ሀገር አፍራሽ ኃይል እኩይ ተግባር እንደምንታገል ቃል እንገባለን፡፡
ከዚህም አለፍ ሲል የአንድነታችን አርማ የሆነው አይበገሬው ጀግናው የሀገር መከላከያ በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተፈጠረውን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደ ነበረበት ለመመለስ የሚያደርገውን ህግ ማስከበር በጽኑ በመደገፍ ከጎኑ መሆናችንን እናረጋግጣለ፡፡
በመጨረሻም በአማራ ክልል እየተከናወነ ያለው የሕግ ማስከበር ተግባር በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ክልሉን ወደ ቀደመው ሰላማዊ እንቅስቃሴው እንደሚመለስ የጋምቤላ ህ/ብ/ክልላዊ መንግሥት ሙሉ እምነቱ ነው፡፡
የጋምቤላ ህ/ብ/ክ/መንግሥት