Fana: At a Speed of Life!

ጃፓን በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ ትብብሮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ቁርጠኝነቷን ገለጸች

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 27፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጃፓኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀያሺ ዮሺማሳ ሀገራቸው በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ ትብብሮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ገለጹ፡፡

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የጃፓኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀያሺ ዮሺማሳ ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ከውይይቱ በኋላም ሁለቱ ባለስልጣናት ለጋዜጠኞች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

የጃፓኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀያሺ ዮሺማሳ በመግለጫቸው እንዳስታወቁት÷ ጃፓን በሁለትዮሽና በዓለም አቀፍ ትብብሮች ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ ናት፡፡

በዚህም ጃፓን በኢትዮጵያ ሰላም ግንባታና ሌሎች የልማት ድጋፎችን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን በበኩላቸው÷ ሁለቱ አገራት የሁለትዮሽ ትብብራቸውን ጨምሮ በቀጣናዊና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ በጋራ በመስራትና ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታዎች ላይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።

የጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀያሺ ዮሺማሳ በኢትዮጵያ ሰላም ግንባታና መልሶ ግንባታ ማቋቋም አገራቸው ድጋፍ እንደምታደርግ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን ኢትዮጵያ ለሁለትዮሽ ግንኙነቱ መጠናከር አበክራ እንደምትሰራ አረጋግጠዋል።

ሁለቱ ወገኖች በቀጣይ በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በልማት ትብብር መስኮች ላይም ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የጃፓኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአፍሪካ አገራት ጉብኝት እያደረጉ ሲሆን ከዚህ ቀደም ደቡብ አፍሪካንና ዩጋንዳን መጎብኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.