በደቡብ ክልል ከማዕድን ልማት ዘርፍ ከ125 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በደቡብ ክልል ባለፈው በጀት ዓመት ከማዕድን ልማት ዘርፍ ከ125 ነጥብ 2 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ መገኘቱ ተገለጸ፡፡
በክልሉ በማዕድን ልማት የተሰማሩ ባለሐብቶች ከ18 ሺህ በላይ ለሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውም ተመላክቷል፡፡
የክልሉ የማዕድን ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አፀደ አይዛ ÷ በክልሉ ለኢንዱስትሪ ግብዓት 125 ሺህ 440 ቶን ማዕድናትን ማምረት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
ከተመረተው ማዕድን 109 ቶን የድንጋይ ከሰል ለሲሚንቶ ፋብሪካዎች ማቅረብ ስለመቻሉም ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።
በበጀት ዓመቱ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ ተተኪ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ግብዓት በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን ማሳደግ የተቋሙ ዋና ዓላማ መሆኑንም ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
በክልሉ ከአርባ ምንጭ፣ ከወላይታ፣ ከዲላ እና ከዋቻሞ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት የማዕድን ጥናት እየተካሄደ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የድንጋይ ከሰል፣ ዶሎማይት፣ ካኦሊን የብረት ማዕድናት እና ሌሎች ተዛማጅ የማዕድን ዓይነቶችን በጥናት መለየት መቻሉም ተብራርቷል፡፡
ማዕድናቱ ለሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች እና ለወጭ ንግድ የሚሆኑ የጌጣጌጥ ማዕድናትን እንደሆኑ በጥናት መረጋገጡን ወ/ሮ አፀደ አይዛ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል።