የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለመፈተን ከልጃቸው ጋር ወደ ዩኒቨርሲቲ ያመሩት የ59 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የ59 ዓመቱ የእድሜ ባለፀጋ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለመፈተን ከልጃቸው ጋር በመሆን ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ አቅንተዋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች ለትምህርት የዕድሜ ገደብ ሲያወጡለት የሚታይ ሲሆን ፥ የዕውቀት ጥምን ለማርካትና ዓላማቸውን ግብ ለማድረስ የትምህርት ተቋማትን ደጅ የሚረግጡም አሉ፡፡
እነዚህ ሰዎች ትምህርት እድሜም ሆነ ሌሎች ተያይዘው የሚመጡ ፈተናዎች ከዓላማቸው ለመድረስ መስዕዋትነትን መክፈል የት ድረስ እንደሆነ አርዓያ በመሆን ያሳያሉ፡፡
የ59 ዓመቱ የእድሜ ባለጸፀጋ ሼሕ ማኑ አባ ጨብሳ አንዱ ናቸው፡፡
በጅማ ዞን ጌራ ወረዳ ዱስታ ከተማም ነዋሪ የሆኑት ሼህ ማኑ ፥ የ10 ልጆች አባት ናቸው፡፡
በልጅነታቸው የሐይማኖት ትምህርት ብቻ የመማር ዕድል ነበረኝ የሚሉት የእድሜ ባለጸጋው ፥ መደበኛ ትምህርት ባለመማራቸው ይቆጩ እንደነበርም ነው የሚያነሱት፡፡
ሆኖም ልጆች ካፈሩ በሗላ የልጅነት ሕልማቸውን ከልጆቻቸው ጋር አብሮ በመማር ማሳካት እንደሚችሉ በማመንና ይህንንም ለማድረግ በመወሰን ጉዟቸውን ተያይዘውታል፡፡
አሁን ላይም በ2015 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲዎች ለሁለተኛ ጊዜ የሚሰጠውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግቢያ የ12ኛ ክፍል ፈተናን ለመፈተን ከልጃቸው ጋር ወደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ አምርተዋል፡፡
በተመስገን አለባቸው