Fana: At a Speed of Life!

በማህበራዊ ሚዲያ በተላለፈ ጥቆማ መነሻነት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 15፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በማህበራዊ ሚዲያ የተላለፈን ጥቆማ መነሻ በማድረግ ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦችን ይዞ ምርመራ እያካሄደ መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ፡፡

በአራዳ ክፍለ ከተማ ከሊፋ ህንፃ አካባቢ የሚንቀሳቀስ ተሽከርካሪን በር በመክፈት ንብረት የሚሰርቁ ወንጀል ፈፃሚዎችን የተመለከተ መረጃ በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱ ተጠቁሟል፡፡

ይህን ተከትሎም በአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የአትክልት ተራ አካባቢ ፖሊስ ጥቆማውን መነሻ አድርጎ ባደረገው ክትትል ሁለት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡

ግለሰቦቹ በከሊፋ ህንፃ፣ በአቡነ ጴጥሮስና በአትክልት ተራ አካባቢ በመንቀስቀስ ወንጀሉን ሲፈፅሙ እንደነበር ተገልጿል፡፡

ከዚህ ቀደም በፈፀሙት ወንጀል አራት እና ሁለት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸው የእስር ግዜያቸውን ጨርሰው የወጡ ደጋጋሚ ወንጀለኞች መሆናቸውንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ተሽከርካሪዎች በዝግታ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት እና በሮች ክፍት መሆናቸውን እንዲሁም አሽከርካሪው ብቻውን መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት ወንጀሉን እንደሚፈፅሙም ነው የተነሰው፡፡

በተለይም ሴት አሽከርካሪዎች ላይ ትኩረት እንደሚያድርጉም ከፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ህዝብ በብዛት በሚንቀሳቀስበት ስፍራ ተመሳሳይ ወንጀል ሲፈፀሙ ሰዎች እየተመለከቱ በዝምታ ማለፋቸው ለወንጀሉ መስፋፋት ምክንያት መሆኑም ነው የተነሳው፡፡

ከዚህ ባሻገርም ለወንጀል ፈፃሚዎቹ ምቹ ሆኔታን እየፈጠረላቸው በመሆኑ ወንጀል ሲፈፀም የሚመለከት ማንኛውም ግለሰብ ወንጀሉን በመከላከል በኩል የድርሻውን ከተወጣ አጥፊዎችን በቀላሉ መቆጣጠር እንደሚቻል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በመጨረሻም ተመሳሳይ የወንጀል ድርጊት ተፈፅሞባቸው ለፖሊስ ያላስታወቁ ግለሰቦች አትክልት ተራ ፖሊስ ጣቢያ በአካል በመቅረብ እንዲያመለክቱም ጥሪ ቀርቧል፡፡

በተጨማሪም በማህበራዊ ሚዲያ ወንጀለኞችን የማጋለጥና መረጃ የመስጠት ልምድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ መልዕክቱን አስተላልፏል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.