ኢንቨስትመንት በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ ተቀዛቅዟል – ተመድ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ባሳለፍነው ዓመት በዓለምአቀፍ ደረጃ ኢንቨስትመንት እጅግ ተቀዛቅዞ መቆየቱን ተመድ አመላከተ፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የንግድና ልማት ስብሰባ ላይ እንደተገለጸው ያለፈው የፈረንጆኡ አመት ዓለም አቀፉ ኢንቨስትመንት በከፍተኛ ደረጃ የተቀዛቀዘበት ነበር።
ሀገራት ጎራ ለይተው በፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጣልቃ እየገቡ ተፅዕኖ ማሳረፋቸው ለዚህ ምክንያት ሆኗልም ነው ያለው የድርጅቱ ሪፖርት።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለሐብቶች መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዳያፈሱ እምነት አሳጥቷቸዋል መባሉን አር ቲ ዘግቧል።
ባሳለፍነው ዓመት የዓለም አቀፉ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በ12 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡
ድርጅቱ ለኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ በምክንያትነት ያቀረበው በዓለም አቀፍ ደረጃ ሲካሄዱ የቆዩ ግጭቶችን እና አለመረጋጋቶችን ነው፡፡
የዩክሬን እና የሩሲያ ግጭት ፣ የምግብ እና የነዳጅ አቅርቦት ዋጋ መናር እንዲሁም ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ የተጫነው የዋጋ ግሽበትም በምክንያትነት ተነስተዋል፡፡
በተመድ የንግድ እና ልማት ዋና ጸሐፊ ሬቤካ ግሪንስፓን ÷ “በዓለምአቀፍ ደረጃ እየጨመረ የመጣው የዋጋ ግሽበት፣ የኢኮኖሚ መውደቅ እና የፋይናንሺያል ገበያዎች አለመረጋጋትን ባለሐብቶች እንደፈለጉ ተዘዋውረው መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዳያፈሱ ማድረጉን እና የዓለምአቀፉን ኢኮኖሚ ማቀዛቀዙን” አንስተዋል።
ይህ መሆኑም የገንዘብ ድጋፍ በሚደረግላቸው በዓለም አቀፍ ፕሮጀክቶች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ከመፍጠሩም በላይ በትላልቅ ኢንዱስትሪዎች ላይ የአቅርቦት መስተጓጎል እንዲፈጠር አድርጓልም ነው ያሉት።