Fana: At a Speed of Life!

የቻይና ባለሐብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እየተሠራ ነው – አምባሳደር ዣዎ ዢዩአን

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 28፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የቻይና ባለሐብቶች በኢትዮጵያ መዋዕለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱ እየተሠራ መሆኑን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣዎ ዢዩአን ገለጹ፡፡

“የቻይና-ኢትዮጵያ ትብብር ለቀጣይ የጋራ ተጠቃሚነት” በሚል መሪ ሐሳብ የቻይና ንግድ ምክር ቤት ያዘጋጀው የቻይና ኩባንያዎች የማሕበራዊ ኃላፊነት ፎረም በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በፎረሙ ላይ የኢፌዴሪ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የቻይና ኤምባሲ ተወካዮች፣ ባለሐብቶች እና የኢንተርፕራይዞች አመራሮች ተገኝተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሥራ ላይ የሚገኙ የቻይና ኩባንያዎች ከመቼውም ጊዜ በላይ ማሕበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቻይና ኢንተርፕራይዞች በተሰማሩባቸው ቦታዎች ለአካባቢ ጥበቃ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እና ለነዋሪዎች ማሕበራዊ እና ምጣኔ-ሐብታዊ ለውጥ የሚጠበቅባቸውን በመወጣት የልማት አጋርነታቸውን ያስቀጥላሉ ሲሉ ገልጸዋል።

ቻይና ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሁሉን አቀፍ ትብብር በሁለትዮሽ፣ በቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ መድረኮችም አጠናክራ እንደምትቀጥል አምባሳደር ዣዎ ዢዩአን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ÷ መንግሰት የውጭ ባለሐብቶችን ለመሳብ እና ምቹ የሥራ አካባቢን ለመፍጠር የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ አቶ አክሊሉ ታደሰ በበኩላቸው÷ የቻይና ባለሐብቶች ለበርካቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለውጭ ገበያ ምርት በማቅረብ የውጭ ምንዛሪን እያስገኙ እንደሆነ ጠቁመው ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢንቨስትመንት እምብርት ለማድረግ በሚደረገውን ጥረት ውስጥ የላቀ ሚና እየተጫወቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የብሔራዊ መልሶ ግንባታ ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ተሾመ ቶጋ÷ ቻይና የኢትዮጵያ ቁልፍ የልማት፣ የንግድ እና የኢንቨስትመንት አጋር መሆኗን በመርሐ-ግብሩ ላይ አንስተዋል፡፡

በወንደሰን አረጋኸኝ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.