Fana: At a Speed of Life!

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና በሙከራ ደረጃ እየተሰጠ ነው

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 23፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመውጫ ፈተና በሙከራ ደረጃ በዩኒቨርሲቲዎች እየተሰጠ መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ሚኒስቴር የአካዴሚክ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) እንደገለጹት÷ፈተናው ከዛሬ ጀምሮ እየተሰጠ ያለው ከ168 ሺህ ለሚበልጡ እጩ ምሩቃን ነው።

የሙከራ ፈተናው ተማሪዎች የራሳቸውን መለያ ቁጥር እና የይለፍ ቃል ተጠቅመው በቀላሉ መፈተን እንዲችሉና ከፈተና ስርዓቱ ጋር እንዲተዋወቁ እንደሚያስችል መሪ ስራ አስፈጻሚው ተናግረዋል።

የሙከራ ፈተናው ፈተና ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን አስቀድሞ ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀና ተማሪዎች የሚገመገሙበትና ውጤቱም የሚያዝ አለመሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

ከሰኞ ሰኔ 26 እስከ ሐሙስ ሰኔ 29 ቀን 2015 ዓ.ም ለሁሉም የግልና የመንግስት ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጥያቄ ክብደቱም ሆነ ብዛቱ ከመውጫ ፈተና ጋር ተመሣሣይ የሆነ ሞዴል ፈተና በተመሳሳይ ጊዜ እንደሚሰጥም ኤባ ሚጀና (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡

እየተሰጠ ባለው የሙከራ መውጫ ፈተና ከኔትዎርክና ከኃይል መቆራረጥ ፣ከመለያ ቁጥርና ይለፍ ቃል መለዋወጥ ከመሳሰሉ ያለፈ የጎላ ችግር አለማጋጠሙንም ተናግረዋል ።

ተማሪዎች ከፈተና ስርዓቱ ጋር በመለማመድና ተገቢውን ዝግጅት በማድረግ ራሳቸውን ለመውጫ ፈተናው ማዘጋጀት እንዳለባቸውም ተገልጿል፡፡

የ2015 ዓም የመውጫ ፈተና ከሐምሌ 3 እስከ 6 ቀን 2015 ዓ.ም በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ለሚገኙ ቅድመ ምረቃ ተማሪዎች በተመሳሳይ ጊዜ እንደሚሰጥ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.