ከአውሮፕላን አደጋ ተርፈው ለ40 ቀናት አማዞን ጫካ ውስጥ የቆዩ አራት ህጻናት በህይወት ተገኙ
አዲስ አበባ ፣ ሰኔ 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮሎምቢያ ከአውሮፕላን አደጋ ተርፈው ለ40 ቀናት በአማዞን ጫካ ውስጥ የቆዩ አራት ህጻናት በህይወት መገኘታቸው ተሰማ።
ህጻናቱ በፈረንጆቹ ግንቦት ወር መጀመሪያ ከእናታቸው ጋር በጉዞ ላይ እያሉ ነበር አውሮፕላኗ አማዞን ጫካ ውስጥ የተከሰከሰችው።
“ሴሴና 206” የተሰኘችው ቀላል አውሮፕላን በሞተር ብልሽት ሳቢያ እንደተከሰከሰችም ነው የተሰማው።
አውሮፕላኗ በወቅቱ አራራኩዋራ ከተባለ ከተማ ወደ ሳን ሆሴ ዴል ጉዋቪያር በመብረር ላይ እንደነበረችም ተገልጿል።
በአደጋው ሳቢያም የህጻናቱ ወላጅ እናት ሁለት አብራሪዎች ህይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ የኮሎምቢያን መከላከያ ጠቅሶ አስነብቧል።
ህጻናቱም በወቅቱ ከአደጋው ተርፈው ጫካ ውስጥ የቆዩ ሲሆን፥ የጠፉትን ህጻናት በህይወት ለመታደግም በርካታ የሀገሪቱ ወታደሮች እና የአካባቢው ነዋሪዎችን ያሳተፈ ፍለጋ ሲካሄድ መቆየቱም ነው የተነገረው።
በፍለጋው አደጋው በደረሰበት ስፍራ የህጻናቱ ወላጅ እናት እና የአብራሪዎቹ አስከሬን ሲገኝ፥ በአካባቢው በተደረገ አሰሳም የህጻናቱ የእግር ኮቴ ሳይሆን አይቀርም የተባለ ዱካ ወታደሮቹና የአካባቢው ነዋሪዎች አግኝተዋል።
ይህን ተከትሎም የ13፣ ዘጠኝ፣ አራት እና የአንድ አመት እድሜ ያላቸውን ህጻናት በህይወት የማግኘት ፍለጋው ላለፉት 40 ቀናት ሲካሄድ ቆይቷል ነው የተባለው።
ከ40 ቀናት አሰሳ በኋላ ህጻናቱ በህይዎት የተገኙ ሲሆን፥ አስፈላጊውን የህክምና ህክምና እንዲያገኙ ወደ መዲናዋ ቦጎታ ተወስደዋል።
ህፃናቱ “ሁይቶቶ” የተባሉና በጫካው አካባቢ ነዋሪ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ማህበረሰብ ተወላጅ መሆናቸውም ነው የተገለጸው።
ይህም ስለ ጫካ ኑሮ እና ፍራፍሬ ያላቸው ግንዛቤ በህይወት እንዲቆዩ ሳያስችላቸው አይቀርም ነው የተባለው።
የኮሎምቢያው ፕሬዚዳንት ጉስታቮ ፔትሮ ህጻናቱ ከተገኙ በኋላ ባስተላለፉት መልዕክት፥ “የህጻናቱ በህይወት መገኘት አስደናቂ ነው፤ በታሪክ ሲወሱ የሚኖሩ የጀግንነት እና የጽናት ተምሳሌት ይሆናሉ” ብለዋል።
ህጻናቱ የተገኙበት የአማዞን ጫካ የአደገኛ እንስሳት መገኛ ሲሆን፥ በተለይም ጃጓር፣ ዘንዶ እና መርዘኛ እባቦች መኖሪያ መሆኑ ይነገራል።