Fana: At a Speed of Life!

የብሪክስ አባል ሀገራት ከምራባውያን የበላይነት ነፃ የሆነ የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር ጠየቁ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሪክስ አባል ሀገራት ሚኒስትሮች ከምራባውያን የበላይነት ነፃ የሆነ የዓለም ስርዓት እንዲፈጠር ጠይቀዋል፡፡

ብራዚል፣ ሩሲያ፣ቻይና፣ህንድ እና ደቡብ አፍሪካን ያካተተው የብሪክስ አባል ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ነው፡፡

የደቡብ አፍሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናሌዲ ፓንዶር በስብሰባ መክፈቻ እንዳሉት ÷የብሪክስ አባል ሀገራት ራዕይ ጂኦፖለቲካዊ ውጥረት፣ ኢ ፍትሃዊነት እና አለመረጋጋት በነገሰበት ዓለም አመራር መስጠትና ከምዕራባውያን የበላይነት የተላቀቀ ስርዓት መፍጠር ነው ብለዋል፡፡

የህንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሱብሃማንያም ጃይሻንካር÷ ስብሰባው በዋናነት ዓለማችን በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንደማትመራ እና አሮጌው የዓለም ስርዓት አሁን ላይ እንደማይሰራ ጠንከር ያለ መልዕክት ለማስተላለፍ ነው ብለዋል፡፡

የብራዚል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማውሮ ቪዬራ በበኩላቸው ÷ብሪክስ የአዳጊ ሀገራትን ፖለቲካዊ ፍላጎት የምታንፀባርቅ የሁሉም የሆነች ዓለም ለመገንባት የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

የቻይናው ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማ ዣኦክሱ የብሪክስ ቡድን በማደግ ላይ የሚገኙ ሀገራትን በማሳተፍ ሊስፋፋ እንደሚችል አስገንዝበዋል፡፡

የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ÷ ሳዑዲ አረቢያን ጨምሮ ከአስር በላይ ሀገራት የብሪክስ አባል ለመሆን ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቁመዋል፡፡

የብሪክስ አባል ሀገራት ከ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን በላይ ህዝብ እንዳላቸው የሚነገር ሲሆን ከጠቅላላው የዓለም ህዝብ 40 በመቶውን እንደሚሸፍኑ ቢቢሲ በዘገባው አስታውሷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.