የቡና ምርትን ልማትና የገቢ መጠን የሚያሻሽል መመሪያ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ ፣ ግንቦት 3 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያን የቡና ምርት ልማትና የገቢ መጠን የሚያሻሽል መመሪያ ማዘጋጀቱን የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን አስታወቀ፡፡
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር)÷ መመሪያው በዘርፉ የእሴት ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙ አካላትን የምርት አቅርቦትና ግብይት የተሻለ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶች የታገዘና በቡና ልማትና ግብይት አስፈላጊ የሚባሉ የአሠራር ስልቶችን ያካተተ በመሆኑ የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
የተዘጋጀው መመሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቡና እሴት ሰንሰለት ውስጥ ያለውን ትብብር ለማጠናከርና ከቡና ንግድ የሚገኘውን ገቢ ለመጨመር የሚያግዝ መሆኑን አብራርተዋል።
በቡና ልማት ለሚሰማሩ አካላት ሥልጠና ለመስጠት የሚያስችል አሠራር ለመዘርጋትና የአነስተኛ አርሶ አደሮችን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ የሚጠቅም መመሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ከቡና ልማት የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ አህጉራዊ የንግድ ትስስርን ማጠናከርና እሴት የተጨመረበትን ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የዘርፉን ልማትና ግብይት በዘመናዊ አሠራር ለማምራት፣ የባለድርሻ አካላትን ትብብር ለማሳደግና የአረንጓዴ ልማትን ለመደገፍ ያግዛል ማለታቸው ኢዜአ ዘግቧል።
በኢትዮጵያ የወጪንግድ ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዘው የቡና ምርት በውጭ ምንዛሬ ግኝት የላቀ ድርሻ እንዳለው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡