ዓለምአቀፉ የምጣኔ ሐብት ውጥረት ካልረገበ አፍሪካ ለጉዳት ትጋለጣለች – አይ. ኤም. ኤፍ
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 25፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በቻይና እና በአሜሪካ ጎራ ተከፍሎ የተካረረው የንግድ ምጣኔ ሐብታዊ ውጥረት ካልረገበ አፍሪካ ለዘላቂ ምጣኔ ሐብታዊ ጉዳት ልትዳረግ እንደምትችል ዓለምአቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) አስጠነቀቀ፡፡
አይ ኤም ኤፍ ይፋ ባደረገው መረጃ ሁለቱን ኃያላን ሀገራት ያማከለው ጂዖፖለቲካዊ ውጥረት እየተባባሰ ከሄደ ÷ የአፍሪካ ሀገራት ከዓለም አቀፉ ገበያ በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ሊስተዋል ይችላል ብሏል፡፡
እንዲሁም የሀገራቱ ዋና የወጪንግድ ገበያ ዕሴት ከዓለምአቀፉ የንግድ ሠንሠለት በከፊል ሊወጣ እንደሚችል ተቋሙ ስጋቱን ገልጿል፡፡
ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት ከ10 ዓመታት በኋላ ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታቸውን በ4 በመቶ ሊቀንሱ እንደሚችሉም ነው ብሉምበርግ የዘገበው፡፡
ወደ ቀጣናው የሚገባው ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት እስከ 10 ቢሊየን ዶላር ሊቀንስ እንደሚችል ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
ከሰሃራ በታች ያሉ ሀገራት የመቋቋም ዐቅማቸውን እንዲገነቡም ኤ ኤም ኤፍ ምክረ ሐሳቡን አስቀምጧል፡፡
ይህን ለማሳካትም የተጀመረውን ቀጣናዊ የንግድ ትሥሥር ማጠናከር የግድ መሆኑን ነው ያነሳው፡፡
የአፍሪካ ሀገራት ከውጭ በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ ጥገኛ ከመሆን ተላቀው የራሳቸውን የፋይናንስ ገበያ እንዲገነቡ እና እንዲያጠናክሩም አይ ኤም ኤፍ አሳስቧል፡፡