የኢትዮ-ፓኪስታን ቢዝነስ ፎረም በቀጣዩ ወር በፓኪስታን ካራቺ ይካሄዳል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 19፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮ-ፓኪስታን ቢዝነስ ፎረም የፊታችን ግንቦት ወር በፓኪስታን ካራቺ ከተማ እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
በፓኪስታን የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀማል በከር ከፓኪስታን ንግድ እና ልማት ባለስልጣን ሊቀ መንበር ዙባይር ሞቲዋላ ጋር ተወያይተዋል፡፡
በውይይታቸውም÷ የኢትዮ-ፓኪስታን ቢዝነስ ፎረም በቀጣዩ ግንቦት ወር ሁለተኛ ሳምንት ላይ በፓኪስታን ካራቺ እንዲካሄድ ተስማምተዋል፡፡
አምባሳደር ጀማል÷የቢዝነስ ፎረሙ የሁለቱን ሀገራት የንግድ ግንኙነት ለማሳደግ እና በንግድ ማህበረሰቡ መካከል ትስስር ለመፍጠር እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡
መድረኩ በሁለቱ ሀገራት ያለውን የንግድ እና ኢንቨስትመንት አማራጭ በማስተዋወቅ ለንግዱ ማህበረሰብ እድሎችን እንደሚፈጥርም አመልክተዋል፡፡
ዙባይር ሞቲዋላ በበኩላቸው÷ የሀገራቱን የንግድ እና ኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማጠናከር ወሳኝ የሆነውን ፎረም ለማስተናገድ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በቢዝነስ ፎረሙ በርካታ የሀገሪቱ ባለሃብቶች እንደሚሳተፉ መግለጻቸውንም ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ፓኪስታን የሚያደርገውን በረራ የፊታችን ግንቦት 9 ቀን የሚጀምር መሆኑም የሀገራቱን የንግድ ግንኙነት ይበልጥ እንደሚያፋጥነው አንስተዋል፡፡