Fana: At a Speed of Life!

የክልል ልዩ ኃይልን መልሰን እናደራጀው እንጂ  እንበትነው አላልንም – ጄነራል አበባው ታደሰ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የክልል ልዩ ኃይልን መልሶ የማደራጀት ተግባር አሁን የተጀመረ ተግባር አይደለም ሲሉ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጦር ሃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል አበባው ታደሰ ገለፁ፡፡

ጄነራል አበባው ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ፥  “የልዩ ኃይል አደረጃጀቶችን መልሶ የማደራጀት ተግባር አሁን የተጀመረ ተግባር አይደለም፤ ለረጅም ጊዜም ጥናት የተደረገበት ነው” ብለዋል፡፡

ጥናቱ የክልሎች ልዩ ሃይሎች ጥንካሬ ምንድነው ብሎ የተመለከተ ሲሆን፥ የክልሎች ልዩ ሃይሎች   ክልላቸውን መጠበቃቸው፣ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር ህይወታቸውን አሳልፈው መስጠታቸውና መሞታቸው፤ እንዲሁም መቁሰላቸውን በጥንካሬ ተመልክቷል ነው ያሉት።

ነገር ግን የልዩ ኃይል አወቃቀሩ ጉድለት እንደነበረው እና ህጋዊም እንዳልነበረም አመልክተዋል።

ከሀገሪቱ ህገመንግስት አንፃር ሲታይ አወቃቀራቸው ህጋዊ አይደለም፤ ህገመንግስቱም እውቅና አይሰጣቸውም ሲሉ ጄነራል አበባው አስረድተዋል።

ይህ ልዩ ሃይል አገነባቡ ብሄር ተኮር መሆኑን በማንሳትም፥ ይህም የህዝቦችን አብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽር መሆኑ ጉድለቱ ነው ብለዋል።

የሀገሪቱን የፖለቲካ መፍቻ መንገድ አበላሽቷል ያሉት ጄነራል አበባው፥ “በምን አበላሸ ለሚለው በእኛ ህገ መንግስት ፖለቲካ እና ጉልበት አብሮ አይሄድም፤ ለዚህም ፖለቲከኛው በሃሳብ ማሸነፍ ሲያቅተው ሌላ በትር አለው ማለት ነው፤ የታጠቀውን ልዩ ሃይል ያነሳል” ሲሉ ነው ያስረዱት።

“ሌላው ልዩ ኃይል ያለበት እጥረት ለሀገር የሚሞተውን ሃይል መገዳደር መቻሉ ነው፤ ተገዳዳሪ ሃይል ተፈጠረ” በማለት ለዚህም እንደምሳሌ ለሁለት ዓመት የቆየውን የትግራይ ጦርነት አንስተዋል፡፡

በጥናቱ ይህ  የክልሎች ልዩ ሃይል ትክክል አይደለም ከተባለ አራት አመት እንደሆነው ነው ያመለከቱት።

“በዚህም ይህንን ሃይል መልሰን እናደራጀው የሚል ውሳኔ ነው  እንጂ የተወሰነው ይበተን፤ ትጥቁን እናስፈታው አልተባለም” ብለዋል።

የሚደራጅበትም መንገድ መከላከያ መግባት ያለበት ወደ መከላከያ፣ ፌደራል ፖሊስ የሚገባው ወደ ፌደራል እንዲገባ እና መደበኛ ፖሊስ መሆን የሚፈልገውም መደበኛ ፖሊስ እንዲሆን ነው የተቀመጠው ሲሉ አብራርተዋል።

ይህም ክብሩን፣ ሞራሉን እና ጥቅሙን  በማይነካ መልኩ እንደሚፈፀም የተያዘው መርሃ ግብር ማስቀመጡን ጠቁመዋል።

“ይህም ምንም ክፋት የለውም፤ ህግ የማስያዝ ነው፤ ጊዜ የሰጠነውም ሌላ ችግር ስለነበረ ነው” ብለዋል፡፡

ሁሉም ክልሎችን ባሳተፈ መልኩ ጥናቱ ላይ ለረጅም ጊዜ ምክክር ተደርጎ የተወሰነ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ይህንን ጥናት ሊያስፈፅም የሚችል ብሄራዊ ኮሚቴ መቋቋም አለበት ተብሎ መቋቋሙን በማከልም ይህም የተደረገው አፈፃፀም ላይ ጉድለት እንዳይኖር በማሰብ መሆኑን ገልፀዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.