Fana: At a Speed of Life!

የጤፍ ምርት ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ በስፋት እንዲገባ እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 16፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከክልሎች ጋር ባደረገው የገበያ ትስስር የጤፍ ምርት ከአማራ ክልል ወደ መዲናዋ በስፋት እንዲገባ እየተደረገ መሆኑን ገለጸ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤፍና ስንዴን ጨምሮ ሌሎች የግብርና ምርቶች ወደ ከተማዋ እንዲገቡ ሲሰራ መቆየቱ ተመላክቷል፡፡

ከዚህ ቀደም ኦሮሚያ ክልል ከሚገኙ የህብረት ስራ ማህበራት ጋር በተደረገ የገበያ ትስስር ወደ ከተማ የገባ የጤፍ ምርት በሸማቾች በኩል በሁሉም አካባቢ ለነዋሪዎች መሰራጨቱ ይታወሳል፡፡

በዛሬው ዕለትም ከአማራ ክልል ምስራቅ ጎጃም ዞን የጤፍ ምርት ወደ አዲስ አበባ ከተማ መግባት መጀመሩን የከተማዋ ንግድ ቢሮ ሃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ቀናትም በዘላቂነት ምርቱ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ከተማ በስፋት የሚገባ መሆኑን ነው ሃላፊው የተናገሩት፡፡

በዛሬው ዕለት የገባው የጤፍ ምርት በሸማች ህብረት ሥራ ማህበራት በኩል ለሁሉም ክፍለ ከተሞች እንደሚሰራጭ መገለጹን የንግድ ቢሮው መረጃ ያመላክታል፡፡

ምንም አይነት እጥረት በሌለበት ደላሎችና ስግብግብ ነጋዴዎች በገበያው ላይ በሚፈጥሩት አለመረጋጋትና በሌሎችም ተያያዥ ምክንያቶች ተከስቶ የነበረውን የጤፍና የስንዴ ምርት የዋጋ ንረት በተሰራው ስራ ውጤት ማሳየቱ ተጠቁሟል፡፡

ህብረተሰቡ በየትኛውም አካባቢ በመዲናዋ የግብርና ምርቶችን የመሰወር እንቅስቃሴዎችን ሲመለከት መረጃ በመስጠት ከቢሮው ጋር በቅንጅት እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.