የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል – አቶ ኦርዲን በድሪ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 29፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሐረሪ ክልል የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እየተከናወኑ የሚገኙ ተግባራትን ማጠናከር ይገባል ሲሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የሐረሪ ክልል ካቢኔ አባላት በቀጣይ 100 ቀናት ሊከናወኑ በታቀዱ ተግባራት ላይ ተወያይተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት÷በክልሉ የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አጠናክሮ ማስቀጠል ይገባል።
በተለይም ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን የህዝብ እንግልት ከማስቀረት አንፃር ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡
ከገቢ አሰባሰብ ጋር በተያያዘም ከደረሰኝና ከተጨማሪ እሴት ታክስ ጋር የሚስተዋሉ ክፍተቶች በመቅረፍ የክልሉን ገቢ የበለጠ ማሳደግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
የዋጋ ንረትን ለማረጋጋትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሌማት ትሩፋትና የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት ስራዎችን እንደ ቁልፍ ተግባር በመውሰድ መንቀሳቀስ ይገባል ብለዋል፡፡
የስራ አጥ ችግርን ለመፍታት የተገነቡ ሼዶችን ወደ ስራ ማስገባት እንደሚገባ ጠቅሰው÷ ፕሮጀክቶች እንዳይጠናቀቁ ማነቆ የሆኑ ጉዳዮችን ለመፍታትና በኢንቨስትመንት ዘርፉ የሚታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ ልዩ ትኩረት መስጠት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በክልሉ በየዘርፉ እየተከናወኑ የሚገኙ አበረታች ተግባራትን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ መግለጻቸውንም ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡