Fana: At a Speed of Life!

ለኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ምላሽ የሚውል የ82 ሚሊየን ዶላር የብድርና እርዳታ ስምምነት ፀደቀ

አዲስ አበባ ፣ ሚያዚያ 2 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ለኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ምላሽ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል ከ82 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር በላይ የብድርና እርዳታ ስምምነትን አፀደቀ።

በዓለም ጤና ድርጅት ዓለም አቀፍ ወረሽኝ የተባለው የኮቪድ-19 በኢትዮጵያ ከመጋቢት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ መከሰቱን የጤና ሚኒስቴር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።
የዳበረ የጤና መሰረተ ልማትና ኢኮኖሚ በሌላቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሃገራት ወረሽኙ የሚያደርሰው ጥፋት የከፋ መሆኑ በባለሙያዎች ሲገለጽ ቆይቷል።

በመሆኑም የወረርሽኙን የጉዳት መጠን ለመቀነስ የኢትዮጵያ መንግስት ከዓለም አቀፍ የልማት ማህበር ለኮሮና ቫይረስ አስቸኳይ ጊዜ ምላሽ ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል 41 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር በእርዳታ እና 41 ነጥብ 3 ሚሊየን ዶላር ደግሞ የብድር ፕሮጀክት መቅረፁን መንግስት አስታውቋል።

ፕሮጀክቱ በጤና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አማካኝነት ለሚቀጥሉት 15 ወራት እንደሚተገበር ነው የተገለጸው።

ፕሮጀክቱ የመድኃኒትና የሕክምና መሳሪያዎች አቅርቦት፣ የጤናው ዘርፍ ዝግጁነት አቅም ግንባታ ስልጠና፣ የማህበረሰብ ውይይቶችና መረጃ ማድረስ እና በቫይረሱ የተያዙትን በለይቶ ማቆያ የማቆየት ተግባራትን ለመፈፀም ያለመ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል።

አጠቃላይ የፕሮጀክቱ ወጪ 82 ሚሊየን 600 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ሲሆን፥ 50 በመቶው በብድር ቀሪው 50 በመቶ ደግሞ በእርዳታ በሚገኝ ገንዘብ ይሸፈናል ነው የተባለው።

ምክር ቤቱም የውሳኔ ሀሳቡን አዋጅ ቁጥር 1190/2012ን መሰረት አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።

በተያያዘ ዜና በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የሚውሉ 2 የብድር ስምምነት አዋጆችም ፀድቀዋል።

የመጀመሪያው በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለሁለተኛው የእድገትና ተወዳዳሪነት የልማት ማስፈፀሚያ የተደረገው የብድር ስምምነት አዋጅ ነው።

ይህም ከዓለም ባንክ የተገኘውን 187 ነጥብ 80 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድር ምክር ቤቱ ያፀደቀ ሲሆን መንግስት እየወሰደ ያለውን የፖሊሲ እርምጃዎች ለመደገፍ እንዲቻል እና የፌደራል መንግስት የ2012 ዓ.ም በጀት በተሟላ ሁኔታ ፋይናንስ ለማድረግ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።

ሌላኛው ደግሞ በኢትዮጵያና በዓለም አቀፍ የልማት ማህበር መካከል ለአፍሪካ የበሽታ መቆጣጠርና መከላከያ ማዕከል ክፍለ አህጉራዊ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ማስፈፀሚያ የሚውል የብድር ስምምነት ነው።

ለዚህ ማስፈፀሚያ የሚውል 150 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ምክር ቤቱ ያፀደቀ ሲሆን 75 ሚሊየን ዶላሩ በእርዳታ ቀሪው 75 ሚሊየን ዶላር ደግሞ በብድር መልክ የተገኘ መሆኑ ተመልክቷል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.