በአምራች ኢንተርፕራይዞች የሚታየውን የሃይል አቅርቦትና የመስሪያ ቦታ እጥረት ለመፍታት እየተሰራ ነው
አዲስ አበባ፣ የካቲት 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በአምራች ኢንተርፕራይዞች ላይ የሚስተዋለውን የሃይል አቅርቦትና የመስሪያ ቦታ እጥረት ለመፍታት በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት አስታወቀ፡፡
የኢንተርፕራይዙ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አብዱልፈታ የሱፍ እንደገለጹት÷ በአነስተኛ እና መካከለኛ አምራች ኢንተርፕራይዞች ላይ የሚስተዋሉ ዋና ዋና ችግሮች በጥናት ተለይተዋል፡፡
በጥናቱ መሰረትም የፋይናንስ፣ የሃይል አቅርቦትና የመስሪያ ቦታ ችግር ለአምራች ኢንተርፕራይዞች ከፍተኛ ተግዳሮት መሆናቸውን ነው የገለጹት፡፡
በሃይል አቅርቦት እጥረት እና በመስሪያ ቦታ ችግርም አምራች ኢንተርፕራይዞች ማምረት ከሚጠበቅባቸው አቅም በታች እያመረቱ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታትም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት መደረጉን አቶ አብዱልፈታ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሃይል አቅርቦት ማስተባበሪያ ሃላፊ አብይ በየነ በበኩላቸው ÷ በአምራች ኢንተርፕራይዞች ላይ ያለውን የሃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በዚህ መሰረትም በሁሉም ክልሎች እና ዲስትሪክቶች የቁልፍ ደንበኞች የአንድ መስኮት አገልግሎት የሚያገኙበት ክፍል በማደራጀት የአምራች ደንበኞችን የሚያስተባብሩ ሰራተኞች መመደባቸውን አንስተዋል፡፡
ደንበኞች የሚጠቀሙትን የሃይል መጠን በመለየት ፈጣን እና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ ቅድሚያ ሊያሰጣቸው የሚያስችል አሰራር መዘርጋቱንም ጠቁመዋል፡፡
አገልግሎቱ በቀጣይ የሃይል መቆራረጥ ችግርን ለመቅረፍ “የዲስትሪቢውሽን ሪሃቢሊቴሽን” ፕሮግራም በማዘጋጀት ፕሮጄክቶችን ቀርጾ እየሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡
የአምራች ተቋማትን በየመስሪያ ቦታ እና የፋይናንስ ችግር ለመቅረፍም ኢንተርፕራይዙ አዲስ ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በመላኩ ገድፍ