Fana: At a Speed of Life!

በዓመት 3 ጊዜ የሚከበረው “ጮዬ ማስቃላ” ዛሬ ይከበራል

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 30፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጋሞ ዞን በዓመት ሦስት ጊዜ የሚከበረው ጮዬ ማስቃላ ዛሬ ይከበራል፡፡

የጋሞ ዞን ባሕላዊ እሴቶች ከሆኑ አንዱና ዋነኛው የ” ዮ ጋሞ ማስቃላ” ዘመን መለወጫ (laytha laame) አንዱ ነው።

“ጮዬ ማስቃላ” በጋሞ ዞን ለየት ባለ መልኩ የሚከበር እጅግ ማራኪ በዓል መሆኑን ከዞኑ ኮሙኒኬሽን ያገኘኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

“ጮዬ” በዳራማሎ ወረዳ ውስጥ ከሚገኙ 24 ቀበሌዎች ውስጥ አንዷ ነች፡፡

ቀበሌዋ ከወረዳው ዋና ከተማ ዋጫ 31 ኪ.ሜ ርቀትና ከጋሞ ዞን መዲና አርባምንጭ በ197 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ትገኛለች።

“የዮ ማስቃላ” በዓል በዞኑ በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች በመስከረም ወር ላይ ይከበራል ።

የ”ጮዬ ማስቃላ” በዓል ግን የራሱን ባሕላዊ የዘመን አቆጣጠር ሥርዓት ተከትሎ በታኅሣሥ ወር የሚከበር የዘመን መለወጫ ነው።

ዳራማሎ ወረዳን ለየት የሚያደርጋት በጋሞ ዞን የመስቀል በዓልን ሦስት ጊዜ የምታከብር ብቸኛ ወረዳ በመሆኗ ነው።

ወረዳዋ በታኅሣሥ ወር የ”ጮዬ ማስቃላን” ፣ በጥቅምት ወር የ”ጉጌ ማስቃላ” እና በአብዛኛው የጋሞ ዞን የሚከበረውን “የዮ ማስቃላ” በዓል በመስከረም ታከብራለች።

ጮዬ ማስቃላ የሚከበረው የደረሰ አዝመራ ከተሰበሰበ በኋላ የሀገር ሽማግሌዎች ቀኑን ቆጥረው በታኅሣሥ ወር ሙሉ ጨረቃ ጥርት ብላ ስትታይ ነው።

“ኢቴ ቶሆ”
የጮዬ ማስቃላ አራት ሳምንት ሲቀረው ባሕላዊ መሪው ከፋንጎ ድቡሻ በዓሉ ስለመድረሱ አዋጅ ያስነግራል ፤ ይህም “ኢቴ ቶሆ” ይባላል።

በዚህ አዋጅ ነጋሪው የሰባቱን ደሬዎች ስም እየጠራ ማስቃላ ደርሷል ይላል።

ቅመም ፣ ቅቤ ፣ ልብስ ፣ ወተት . . . ግዙ የተጣላችሁ ታረቁ እያለም መልዕክቱን ያስተላልፋል።

“ሶፌ”

በዚህ ዕለት ዓመቱን ሙሉ ያገቡ ሙሽሮች ፣ ግዳይ የጣሉ ጀግኖች ፣ አራስ ሴቶች ፣ አዲስ ባሕላዊ ሹመት የተቀበሉ ሁሉ ዕውቅና የሚያገኙበት እና ከማኅበረሰቡ የሚቀላቀሉበት ሥርዓት ነው።

“ካሎ ዲሾ”

ዕለተ አርብ “ካሎ ዲሾ” ይባላል ፤ ከብቶች እስከ ማስቃላ ተጠብቆ የቆየ ለምለም የግጦሽ ሣር እንዲግጡ ይፈቀዳል። ቅዳሜ እርድ ነው። ዕሑድ /Tama keso/ ደመራ ይደመራል።

ዕለተ ዕሑድ ከንጋቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ ነዋሪዎች ከሕጻን እስከ አዋቂ ችቦ በመያዝ ወደ ፋንጎ ይተማሉ።

በየመንገዱ ከቤት ለኩሰው ባወጡት ችቦ አንዱ አንዱን እየነካ “ዮ ዮ ማስቃላ”እየተባባሉ መልካም ምኞታቸውን በመግለጽ ፋንጎ አደባባይ ሲደርሱ ችቧቸውን ያከማቹና ወደ ቤት ይመለሳሉ።

“ጉጌኖ”

ጉጌኖ የማስቃላ ችቦ በወጣ በሳምንቱ ዕሁድ የሚከናወን የሽኝት ሥነ ስርዓት ነው።

ከማለዳ እስከ ስድስት ሰዓት ሲበላ ሲጠጣ ይዋልና ልክ ሰባት ሠዓት ላይ በአራቱም አቅጣጫ የበዓሉ ሰዓት መድረሱን የሚያበስር “ዛዬ” ይነፋል።

በዚህ ጊዜ በሰባቱም ቀበሌዎች ያሉ “ሀለቃዎች” እና “ሁዱጋዎች”ከሰጎን ላባ የሚዘጋጅ ” ጉቼ” በየሀብት መጠናቸው ቁጥር ልክ በእንሰት ኮባ ላይ ሰክተው በጭንቅላታቸው ላይ አስረው የሐገር ሽማግሌዎች በቡድን በቡድን ሆነው በአራት አቅጣጫ ወደ ፋንጎ አደባባይ በመምጣት ኡደት ያደርጋሉ።

መሸት ሲል ከየአካባቢው የመጣ ችቦ ይደመርና በ”ጮዬ ኤቃ” አማካይነት ደመራው ይለኮሳል።

ደመራው ሲቀጣጠል ወጣቶች እሳቱን እየዞሩ ባሕላዊ ጨዋታ ይጫወታሉ።

በመጨረሻም በ”ፋንጎ ድቡሻ” ማሳረጊያ ምርቃት በአባቶች ይደረጋል።

ሁሉም ይነሱና “ዮ ዮ ማስቃላ” በማለት ጉጌኖ !ጉጌኖ ! እያሉ ወደ ፋንጎ ይመለሱና የበዓሉ ፍጻሜ ይሆናል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.