ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሐረሪ ክልል በይፋ ተጀመረ
አዲስ አበባ ፣ ታኅሣሥ 22 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በሐረሪ ክልል በይፋ ተጀመረ።
ንቅናቄውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስጀምረዋል።
ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ በማምረት ላይ ያልነበሩ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ እንዲገቡና ያመርቱ የነበሩትም የምርት መጠናቸው እንዲጨምር ማስቻሉን አቶ ኦርዲን በድሪ አመላክተዋል።
ይህን ተሞክሮ እንደ ክልል በመውሰድ ለኢንዱስትሪው እድገት መስራት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱንም ገልፀዋል።
በመሆኑም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን በመመስረት ሐረር ታምርት በሚል መርህ ወደ ስራ መገባቱን አስታውቀዋል።
በክልሉ ኢንዱስትሪን ለማሳደግ ማነቆ የሆኑትን የህግ ማስከበር፣ የወሰን፣ የካሳና የአደረጃጀት ተግዳሮቶች እንዲፈቱ ይሰራልም ነው ያሉት።
የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አስፋው አበበ በበኩላቸው፥ ክልሎች ለንቅናቄው መሳካት አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር መቻል አለባቸው ብለዋል።
የሐረሪ ክልል ኢንተርፕራይዞችና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ሠሚራ ዩሱፍ ሐረር በ1950ዎቹ ከኢንዱስትሪ ጋር መተዋወቋን አመላክተዋል።
ይሁንና በሚጠበቀው መልኩ ኢንዱስትሪውን ማሳደግ ባለመቻሉ ዛሬ ላይ በክልሉ ከ60 ያልተሻገሩ ኢንዱስትሪዎች ብቻ መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ይህንን ክፍተት ከመሙላት አንፃርም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ መጀመሩ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት አመላክተዋል።
በእዮናዳብ አንዱዓለም