የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የፌደራል ተቋማትን ለመጠበቅ መቀሌ ገባ
በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት መሠረት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት የሚተዳደሩ ተቋማትን ለመጠበቅ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በዛሬው ዕለት ትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ገብቶ ሥራ መጀመሩን ገለፀ፡፡
መንግስትና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የደረሱባቸውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በትግራይ ክልል የሚገኙ በኢ.ፌ.ዲ.ሪ መንግስት የሚተዳደሩ አየር ማረፊያዎች፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የቴሌኮም አገልግሎት፣ የባንክና ሌሎች ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ የፌደራል ተቋማት አስተማማኝ ጥበቃ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ቀደም ብሎም በትግራይ ክልል አካባቢዎች በመግባት ህብረተሰቡን በማረጋጋት ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ በማድረግ የፀጥታና ደህንነት የማስከበር ስራዎችን እየሰራ መቆየቱ ይታወቃል።