ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 20፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት በተለያዩ ስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መስራት የሚያስችላቸውን የመግባቢያ ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አድማሱ ዳምጠው እና የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና ተፈራርመዋል።
ሁለቱ ተቋማት የተፈራረሙት ስምምነት በቴክኖሎጂ የታገዘ የመረጃ አሰባሰብ እና አያያዝ እንዲኖር የሚያግዝ መሆኑም በፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ ተጠቁሟል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ወርቁ ጋቸና ስምምነቱ ወጣቱን በቴክኖሎጂ በማገዝ ችግር ፈቺ ስራዎችን ለማከናወን ኢንስቲትዩቱ እያደረገ ያለውን ጥረት በሚዲያ ለማገዝ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ፋና በሚዲያ ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቁ ተቋም ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፥ ስምምነቱ ኢንስቲትዩቱ ያበለፀጋቸውን ቴክኖሎጂዎች ተጠቅሞ አሰራሩን እንዲያዘምን ያስችላል ነው ያሉት።
ወጣቱ ትውልድ ስለ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ እንዲያውቅ እና አውቆም ቴክኖሎጂ እንዲፈጥር ለማስቻል በፋና በኩል ለመድረስ እንደሚያስችል አመልክተዋል።
የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለፋና ልዩ ልዩ እገዛ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቅሰው ምስጋና አቅርበዋል።
ቴክኖሎጂው እያደገ እና እየረቀቀ በመጣበት በዚህ ዘመን በመረጃ የዳበረ ብቁ ዜጋን ለመፍጠር እና የሚዲያ ተቋሙ የሚሰራውን ስራ ውጤታማ ለማድረግ የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስን ከመሰሉ ተቋማት ጋር መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
የዛሬው ስምምነት በዚህ የመረጃ እና የዲጂታል ዘመን ፈተና ሆኖ የመጣውን የሀሰት መረጃ ስርጭትን ለመግታት፣ የሚዲያ አሰራርን ለማዘመን እና በአጠቃላይ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችል ነው ብለዋል።
በሠሎሞን ይታየው እና ሀይለማርያም ተገኝ