Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ዓየር መንገድ ከነገ ጀምሮ ወደ መቀሌ መደበኛ በረራ ይጀምራል

አዲስ አበባ፣ ታኅሣሥ 18፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአዲስ አበባ መቀሌ ከነገ ጀምሮ ዳግም በረራ እንደሚጀምር የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስታወቀ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈጻሚ መስፍን ጣሰው ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ፥ ተቋርጦ የነበረው ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ የአየር ትራንስፖርት በነገው ዕለት ይጀምራል ፡፡

በፌዴራል መንግስቱና በህወሓት መካከል የተደረገውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ የአቬየሽን ሰራተኞች ወደ መቀሌ አቅንተው የመቀሌ አየር መንገድ ለበረራ ምቹ ሁኔታ ላይ መሆኑን አረጋግጠዋልም ነው ያሉት።

በመሆኑም ነገ በሚጀምረው በረራ በቀን አንድ ጊዜ የሚካሄድ መሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን ፥ የደንበኞቹ ፍላጎትን መሰረት በማድረግም የበረራው ቁጥሩ ከፍ ሊል የሚችልበትን ሁኔታ እንደሚፈጠርም ነው ዋና ስራ አሰፈጻሚው የገለፁት፡፡

ተቋርጦ የነበረውን የበረራ እንቅስቃሴ በሁሉም የትግራይ ክልል የበረራ መዳረሻዎች ለማስጀመር ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ዋና ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል፡፡

ነገ የሚጀምረው በረራም ከሌላው ወገኑ ጋር ግንኙነቱ ተቋርጦ የነበረውን የትግራይ ህዝብ ዳግም እንዲገናኝ ለማድረግ ትልቅ እድል የሚፈጥር እንደሆነም ነው የተናገሩት።

ከዚህ ባለፈ የሸቀጦችና ሌሎች ተደራሽ የመሆን እጥረት የነበረባቸውን የሰብዓዊ ድጋፎችን በበቂ ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ከፍ ማድረግ የሚያስችል እንቅስቃሴ መሆኑንም ዋና ስራ አስፈፃሚው በመግለጫቸው ገልፀዋል፡፡

በይስማው አደራው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.